ሩስያ ዩክሬንን ከወረረች ፑቲን ላይ ማዕቀብ እንደሚጣል ባይደን አስጠነቀቁ

ታትሟል

ሩስያ ዩክሬንን ከወረረች የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ላይ ማዕቀብ እንደሚጣል የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስጠነቀቁ።

ሩስያ በደቡብ ምዕራብ ድንበሯ ያለችውን ዩክሬንን ከወረረች "ትልቅ ቅጣት" እንደሚከተል ባይደን አሳስበዋል።

ሌሎች የምዕራቡ ዓለም አገራትም ሩስያን እያስጠነቀቁ ይገኛሉ።

ሩስያ ዩክሬንን የመውረር ዕቅድ የለኝም ብላ አሜሪካ እና ሌሎችም አገራት "ነገሩን እያጋጋሉ" ነው ስትል ትወቅሳለች።

ሩስያ ይህን ብትልም ድንበሯ ላይ ወደ 100,000 ወታደሮች አሰማርታለች።

ሩስያ ዩክሬንን ከወረረች በቀጥታ ፑቲን ላይ ያነጣጠረ ማዕቀብ እንደሚጣል ነው ባይደን ያስጠነቀቁት። ሩስያ ዩክሬንን ከወረረች "ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ትልቁ ወረራ" ይሆናል ብለዋል።

የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን (ኔቶ) በምሥራቅ አውሮፓ ጠንካራ ክትትል እንደሚያደርግ ጠቅሰው "የትኛውም የኔቶ አባል ጥቃት ሲሰነዘርበት ኔቶ ይከላከለዋል" ሲሉ ተደምጠዋል።

አሜሪካ ወታደሮቿን ወደ ዩክሬን የመላክ ዕቅድ እንደሌላት ባይደን በተደጋጋሚ ተናግረዋል።

ሩስያ በበኩሏ አሜሪካ እና ኔቶ ዩክሬንን በምዕራባውያን አማካሪዎች እና በጦር መሣሪያ "አጥለቅልቀዋታል" ስትል ከሳለች።

በተባበሩት መንግሥታት የሩስያ ቋሚ መልዕክተኛ "ሩስያ ድንበር አካባቢ አሜሪካውያኑ ምን እያረጉ እንደሆነ ግልጽ አይደለም" ሲል መግለጫ አውጥቷል።

ሩስያ የነዳጅ መስመር የምትቆርጥ ከሆነ ዝግጁ ሆኖ ለመጠበቅ የመላው ዓለም ነዳጅ አቅራቢዎች ወደ አውሮፓ የሚልኩትን ነዳጅ እንዲጨምሩ ባይደን ጠይቀዋል።

የአውሮፓ ሕብረት ከሚያስገባው ድፍድፍ ነዳጅ አንስ ሦስተኛውን የምትልከው ሩስያ ናት።

የዩናይት ኪንግደሙ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን፤ የምዕራቡ ዓለም አገራት ሩስያ ላይ "ከባድ" የምጣኔ ሀብት ማዕቀብ እንደሚጥሉና አገራቸውም የኔቶ አባላትን ለመደገፍ ወታደሮች እንደምትልክ ተናግረዋል።

ሩስያ ከዓለም አቀፉ የክፍያ ሥርዓት ስዊፍት እንደምትታገድ ቢናገሩም፤ በምላሹ የሩስያ ባለሥልጣናት አውሮፓ የሩስያን ምርቶች ገዝታ የምትከፍልበት ሥርዓት አይኖራትም ሲሉ አስፈራርተዋል።

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ከሩስያ ጋር ውይይት በማድረግ እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

አሜሪካ 8,500 ወታደሮቿ በተጠንቀቅ እንዲጠብቁ ማዘዟን ሩስያ "እጅግ አስጊ" ብላዋለች።

አሜሪካ ከሩስያ በተጨማሪ የሩስያ አጋር የሆነችውን ቤላሩስም አስጠንቅቃለች።

ሩስያ በበኩሏ ኔቶ ወደ ምሥራቅ የሚያደርገው መስፋፋት ያሰጋኛል ትላለች።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲማይር ዘለንስኪ በቴሌቭዥን ቀርበው ሕዝባቸውን ለማረጋጋት ሞክረዋል።

"ሁሉም ነገር ቀላል ባይሆንም ተስፋ አለ። አካላችሁን ከቫይረስ፣ አእምሯችሁን ከውሸች፣ ልባችሁን ከፍርሃት ተከላከሉ" ብለዋል።

ሩስያ እአአ በ2014 ክሬሚያን በግድ የግዛቷ አካል አድርጋለች።

ክሬሚያ በሩስያ ግዛት ውስጥ ለመቆየት በሕዝበ ውሳኔ ስትወስን ዩክሬን ግን ሕገ ወጥ ስትል ሐሳቡን ውድቅ አድርጋለች።