በመድፈር ወንጀል የተከሰሰው ክሪስ ብራውን የ20 ሚሊየን ዶላር ካሳ ተጠየቀ

ክሪስ ብራውን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ክሪስ ብራውን
ታትሟል

አሜሪካዊው ድምጻዊ ክሪስ ብራውን አንዲት ሴትን አደንዛዥ ዕፅ በመስጠት እና በመድፈር ክስ የተመሰረተበት ሲሆን የ20 ሚሊየን ዶላር ካሳ ጥያቄ ቀረበበት።

ክሪስ ብራውን የተጠረጠረበት ጥቃት ከአንድ ዓመት በፊት በታኅሣሥ ወር በማያሚ፣ ፍሎሪዳ ውስጥ በመዝናኛ ጀልባ ላይ እንደተፈፀመ ተዘግቧል።

በጉዳዩ ላይ ዘገባ ሰራው 'ሬዲዮ ዋን ኒውስቢት' የክሪስ ብራውንን ማናጀሮች አስተያየት ለማግኘት ቢሞክርም እስካሁን ምላሽ አልተሰጠውም።

ክሪስ ብራውን በኢንስታግራም ላይ ምላሽ ለመስጠት የሞከረ ሲሆን የቀረበበት ክስ አዲስ ሙዚቃ ሊቀለቅ በዝግጅት ላይ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የመጣ እንደሆነ አመልክቷል።

"ይህንን በተደጋጋሚ የሚደረግ ነገርን ሁላችሁም እየተመለከታችሁት እንደሆነ ተስፋ አደርጋለሁ። ሁልጊዜ አዲስ ሙዚቃ ወይም ፕሮጀክት ልለቅ ስል" የሚመከሰት ነገር እንደሆነ የሚገልጽ ጽሁፍ አስፍሯል።

ክሱ የተመሰረተው እስካሁን ማንነቱ ይፋ ባልወጣ ሙዚቀኛ እና የዳንስ ባለሙያ ሲሆን በሕጋዊ ሰነዶች ውስጥ "ጄን ዶ" በሚል ስም ብቻ ተጠቅሷል።

ሰነዶቹ በዘፋኙ ላይ አምስት የተለያዩ ክሶችን የሚዘረዝሩ ሲሆን ፆታዊ ጥቃት፣ የፀረ ፆታዊ ጥቃት ሕግን መጣስ፣ ሆን ብሎ የስሜትን ማቃወስ፣ በቸልተኝነት ስሜትን ማቃወስ እና ሐሰተኛ እስራት የሚሉ ናቸው።

ከሳሽ "ለህይወቷ እና ለሥራዋ እንደምትፈራ" በመግለጽ በሰነዱ ላይ ስጋቷን አስፍራለች።

ጥቃቱ ተፈጽሞበታል ወደተባለው የመዝናኛ ጀልባ የሄደቸውም በጀልባዋ ባለቤት የሆነው የራፕ ሙዚቀኛው እና ፐሮዲዩሰር ዲዲ ተጋብዛ መሆኑንም አክላለች።

ኒውስቢት አየሁት ባለው የክስ ሰነድ መሰረት ግለሰቧ ወደ ጀልባዋ ከሄደች በኋላ ክሪስ ብራውን መጠጥ እንድትጠጣ እንደጋበዛት እና ከዚያ በኋላ "ድንገተኛ እና ልገልጸው የማልችለው ለውጥ አእምሮዬ ላይ ተሰማኝ" ስትል ገልጻለች።

ከዚያም "ግራ መጋባትና፣ አካላዊ አለመረጋጋትና እንቅልፍ ወደ ሚመስል ስሜት ውስጥ መግባት እና መውጣት አጋጠመኝ" ስትል ክሪስ ልብሷን በማውለቅ የመድፈር ጥቃት ወደፈጸመበት መኝታ ክፍል እንደተወሰደች ክሰተቱን አብራርታለች።

ሰነዱ ክሪስ ብራውን ግለሰቧን በማግስቱ እንዳገኛት እና የድንገተኛ የእርግዝና መከላከያ እንድትወስድ እንደነገራትም ያትታል። ኒውስቢት የፕሮዲዩሰሩን የዲዲ ተወካዮች በማግኘት አስተያየታቸውን ምላሻቸውን ቢጠይቅም እስካሁን ምላሽ አላገኘም።