ከኮቪድ ክትባት በኋላ የሚከሰት የወር አበባ ለውጥ ቶሎ እንደሚስተካከል ተገለጸ

ካላንደር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ከኮቪድ-19 ክትባት በኋላ የወር አበባ ዑደት ላይ መጠነኛ ለውጥ እንደሚከሰት፣ ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ ወደ መደበኛ ዑደት እንደሚመለስ ባለሙያዎች አስታወቁ።

በዩናይትድ ኪንግደም እውቋ የወር አበባ ባለሙያ ዶ/ር ቪክቶርያ ሜል እንዳሉት፤ በአሜሪካ እና ኖርዌይ የተሠሩ ጥናቶች ከኮቪድ ክትባት በኋላ የሚቀየረው የወር አበባ ዑደት እንደሚመለስ አመልክተዋል።

የኮቪድ-19 ክትባት ወሊድ ላይ እክል ሊያስከትል ይችላል የሚለው የተሳሳተ ወሬ ሳይንሳዊ መሠረት እንደሌለውም ዶክተሯ ተናግረዋል።

የዩኬ የጤና እንክብካቤ ክፍል የደረሱት ከ37,000 በላይ የስልክ ጥሪዎች እንደሚያመለክቱት ከኮሮናቫይረስ ክትባት በኋላ የማሕጸን መድማት፣ የወር አበባ መዝየት ወይም በወር አበባ ወቅት ከፍተኛ ደም መፍሰስ የገጠማቸው አሉ።

የሴቶች የወር አበባ ዑደት እና መጠን የተለያየ በመሆኑ ሁሉም ሪፖርት ከክትባቱ ጋር የተገናኘ ሊሆን እንደማይችል ያመኑት ባለሙያዎች ተጨማሪ ምርመራ ለማድረግ ተስማምተዋል።

አሜሪካ ውስጥ በመተግበሪያ የወር አበባ ዑደታቸውን የሚከታቱ 4,000 ሴቶች እንዳሉት፤ ከመጀመሪያው የኮቪድ-19 ክትባት በኋላ የወር አበባቸው ላይ ለውጥ ባይታይም፣ ከሁለተኛው ዙር ክትባት በኋላ የወር አበባቸው በግማሽ ቀን ዘግይቷል።

በአንድ የወር አበባ ዑደት ውስጥ ሳሉ ሁለቱም ዙር ክትባት የወሰዱ ሴቶች ደግሞ ቀጣይ የወር አበባቸው በሁለት ቀናት ዘግይቷል።

በዩኬ፤ ከአሥር ሴቶች አንዷ ከክትባት በኋላ የወር አበባዋ ከስምንት ቀናት በላይ እንደዘገየ ገልጸዋል።

ይህ ካልተከተቡ 25 ሴቶች አንዷ የሚገጥማት ነው። ከሁለት የወር አበባ ዑደት በበኋላ ግን ወደ መደበኛው ይመለሳል።

ኖርዌይ ውስጥ የተሠራው ጥናት 5,600 ሴቶችን ያካተተ ነው።

40% ከመከተባቸው በፊትም የወር አበባቸው በተለያየ ጊዜ ይለዋወጥ ነበር። ይህም ከፍተኛ ደም መፍሰስን ይጨምራል።

ዶ/ር ቪክቶርያ "ከክትባት በኋላ የወር አበባ ዑደት ይከሰታል። ግን በቀላሉ ይስተካከላል። ክትባቱ መኻንነት ያስከትላል የሚለው ሐሰተኛ ወሬ ነው" ብለዋል።

እንዲያውም በኮሮናቫይረስ መያዝ የወንድ ፍሬ መጠን እና ጥራት ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ዶክተሯ ገልጸዋል።