ጁሊያን አሳንጅ ለአሜሪካ ተላልፎ እንዲሰጥ የተላለፈው ውሳኔ ላይ ይግባኝ እንዲጠይቅ ተፈቀደለት

ታትሟል

የዊክሊክስ መስራች ጁሊያን አሳንጅ ለአሜሪካ ተላልፎ እንዲሰጥ የተላለፈበት ውሳኔን በመቃወም ባደረገው የፍርድ ቤት ክርክር አሸነፈ።

በመሆኑም አሳንጅ ከዩናይትድ ኪንግደም ተላልፎ ለአሜሪካ እንዲሰጥ የተላለፈበትን የፍርድ ቤት ውሳኔን በመቃወም ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ይግባኝ ለመጠየቅ መብት አግኝቷል።

ጁሊያን በአውሮፓውያኑ 2010 እና 2011 በሺዎች የሚቆጠሩ ምስጢራዊ ሰነዶችን በድረ ገጹ ላይ ይፋ በማውጣትና በማተም በአሜሪካ በጥብቅ ይፈለጋል።

አሳንጅ በዊኪሊክስ ድረ ገጽ ላይ የታተሙ ከአፍጋኒስታንና ከኢራቅ ጦርነቶች ጋር የተያያዙ ምስጢራዊ መረጃዎችን ወታደራዊ የመረጃ ቋት ሰብሮ በመግባት ለመውሰድ ከማሴር ጋር በተያያዘ በአሜሪካ መንግሥት በርካታ ክሶች ቀርበውበታል።

ታኅሣሥ ወር ላይ ከዚህ ቀደም የዩናይትድ ኪንግደም ፍርድ ቤት ከጁሊያን የአዕምሮ ጤና ላይ ባላቸው ስጋት ለአሜሪካ ተላልፎ ሊሰጥ እንደማይችል ባሳለፈው ውሳኔ ላይ አሜሪካ ባቀረበችው ይግባኝ ማሸነፍ ችላ ነበር።

የዊክሊክስ ምስጢራዊ ሰነዶች የአሜሪካ ጦር በአፍጋኒስታን በነበረው ጦርነት ወቅት ባልተዘገበና ባልተገለጸ ሁኔታ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎችን እንዴት እንደገደለ አጋልጧል።

በተጨማሪም ሾልከው የወጡ የኢራቅ ጦርነት ሰነዶች ደግሞ 66 ሺህ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውንና እስረኞች በኢራቅ ኃይሎች እንደተሰቃዩ አሳይተዋል።

አሜሪካ ሾልከው የወጡት መረጃዎች ሕግ የሚጥሱ እና ሕይወትን አደጋ ላይ የሚጥሉ ናቸው ብላለች።

ጁሊያን በበኩሉ ክሱ ከፖለቲካ ጋር የተያያዘ ነው ብሏል።