ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዊኪሊክሱ መስራች ጁሊያን አሳንጅ በእስር ላይ ሆኖ ሊሞሸር ነው
የዊኪሊክስ መስራቹ ጁሊያን አሳንጅ ከረዥም ግዜ አጋሩ ስቴላ ሞሪስ ጋር በሚገኝበት የቤልማሪሽ ማረሚያ ውስጥ ሆኖ ትዳር እንዲመሰርቱ ፈቃድ አገኙ።
ጥንዶቹ አሳንጅ ለንደን በሚገኘው የኢኳዶር ኤምባሲ ውስጥ ተጠልሎ በነበረ ግዜ የተጸነሱ ሁለት ልጆች እንዳሏቸው ሞሪስ ተናግራለች።
የማረሚያ ቤቶቹ አስተዳደር በበኩሉ የአሳንጅ ማመልከቻ በተለመደው የማረሚያ ቤቱ አሠራር መስተናገዱን ተናግሯል።
ታራሚዎች ጋብቻ መፈጸም ሲፈልጉ ማመልከቻቸውን ካቀረቡ እና ከጸደቀ በኋላ የጋብቻቸውን ሙሉ ወጪ በመሸፈን መጣመር እንደሚችሉ በሕግ የተደነገገ ነው።
«ከዚህ በኋላ በትዳራችን ውስጥ ጣልቃ ገብነት እንደማይኖር ተስፋ አደርጋለሁ። ምክንያታዊነት በመጨረሻ በማሸነፉ እረፍት ተሰምቶኛል» በማለት ስቴላ ሞሪስ ተናግራለች።
የደቡብ አፍሪካ ተወላጅ በሙያዋ ጠበቃ የሆነችው ሞሪስ ከአንድ አመት በፊት ከአሳንጅ ጋር እአአ ከ2015 ጀምሮ በፍቅር ግንኙነት ውስጥ መቆየታቸውን እና ያፈሯቸውን ሁለት ልጆችም ለብቻዋ እያሳደገች እንደሆነ ለሜይል ተናግራ ነበር።
ሞሪስ በዊኪሊክስ የዩትዩብ ገጽ ላይ በተጋራው ቪዲዮ ላይ ከአሳንጅ ጋር እአአ በ2011 የጠበቆች ቡድኑን በተቀላቀለችበት ወቅት መተዋወቃቸውን ተናግራ ነበር።
አክላም በኤምባሲ ውስጥ ተጠልሎ በነበሩበት ወቅት በየቀኑ ስትጎበኘው እንደነበረ እና ይህም ጁሊያንን ለማወቅ ዕድል እንደሰጣት ተናግራለች።
ልጆቻቸው ሲወለዱም አሳንጅ በቪዲዮ መመልከቱን እና ልጆቹም አባታቸውን በኤምባሲ በመገኘት በተደጋጋሚ መጎብኘታቸውን ትናገራለች።
የ50 ዓመቱ አሳንጅ በስለላ ወንጀል ተጠርጥሮ ወደሚፈለግበት አሜሪካ ተላልፎ ላለመሰጠት በመሟገት ላይ ይገኛል።
በዜግነት አውስትራሊያዊ የሆነው አሳንጅ እአአ በ2019 ተጠልሎ ከሚገኝበት የኢኳዶር ኤምባሲ በለንደን ፖሊስ ተይዞ ወደ ቤልማሪሽ ማረሚያ መወሰዱ ይታወሳል።
ይህም የነበረውን የዋስትና ቅድመ ሁኔታዎች በመጣሱ ምክንያት እንደሆነም በወቅቱ ተገልጾ ነበር።
በኤምባሲው ውስጥ የተጠለለው በስዊዲን የጾታዊ ጥቃት ክስ ከቀረበበት በኋላ ተላልፎ ላለመሰጠት ነበር። ክሱ የሐሰት ነው በማለት ሲከራከሩ ቆይተው በመጨረሻም ውድቅ ሆኗል።