በንቅለ ተከላ ህክምና የአሳማ ልብ ያገኘው ግለሰብ ከአመታት በፊት አንድን ሰው ለሞት አድርሷል ተባለ

ዴቪድ ቤኔት

የፎቶው ባለመብት, University of Maryland School of Medicine

ታትሟል

በአለማችን በንቅለ ተከላ ህክምና በዘረ መል ምህንድስና የተሻሻለ የአሳማ ልብ ያገኘው የመጀመሪያው ግለሰብ ከአመታት በፊት አንድን ግለሰብ በስለት ሰባት ጊዜ ወግቶ ለሞት አድርሶት እንደነበር የተጎጂው ቤተሰቦች ገለጹ።

ግለሰቡ በህይወት ቢተርፍም መንቀሳቀስ አይችልም ነበር።

የ57 አመቱ ዴቪድ ቤኔት በአውሮፓውያኑ 1988 ኤድዋርድ ሹሜከርን በስለት በመውጋት ወንጀል ጥፋተኛ ተብሎ እንደተፈረደበትም እህቱ ለ4ስ ቱደይ ሾው ተናግራለች።

እህቱ ሌስሊ ሹሜከር ዳውኒ እንዳለችው ወንድሟ ጥቃቱን ተከትሎ ባጋጠመው ችግር ለሁለት አስርት አመታት ሲሰቃይ ቆይቶ በአውሮፓውያኑ 2007 ህይወቱ አልፏል ብላለች።

የመጀመሪያውን የአሳማ ልብ በንቅለ ተከላ ያገኘው ቤኔት የዚህ ፈር ቀዳጅ ቀዶ ህክምና ተጠቃሚ ሊሆን ባልተገባም ነበር ስትል እህቱ ታስረዳለች።

ነገር ግን ቀዶ ህክምናውን ያከናወነው ቡድን የአንድ ሰው የወንጀል መዝገብ ህክምናን ለመከልከል በፍፁም ምክንያት ሊሆን አይችልም ብሏል።

ጥቃቱ የተፈፀመው በአውሮፓውያኑ 1988 ሲሆን የቤኔት ባለቤት በሽሜከር ጭን ላይ መቀመጧንም ተከትሎ ነው።

በቅናት መንፈስ የነደደው ቤኔት ሽሜከርን ከጀርባው ደጋግሞ ሰባት ጊዜ በስለት ወግቶታል።በወቅቱ ወንድሟ የ22 አመት ወጣት ነበር።

በወቅቱም ቤኔት ባደረሰው ጥቃት እና መሳሪያ በመያዝ የ10 አመት እስር ተፈርዶበታል።

ቤኔት የአሳማ ልብ ሊያገኝ እንደሆነ ማንም እንዳልነገራትና ዜናውንም የሰማችው ከልጇ እንደሰማች እህቱ ገልጻለች።

"ሁለተኛዋ ልጄ 'እማዬ፣ አጎቴን ኢድን የወጋው ይህ ሰው ነው ብላ መልእክት ላከችልኝ" ከዚያም ታሪኩን ሳነብ ልቡን መቀበሉ በጣም አናደደኝ" ብላለች

ቤኔት ሰባት ሰዓት ከፈጀው የሙከራ ቀዶ ህክምና በኋላ በማገገም ላይ ነው።

ንቅለ ተከላው የቤኔትን ህይወት የማዳን የመጨረሻ ተስፋ ተደርጎ የተወሰደ ቢሆንም ለረጅም ጊዜ በህይወት የመቆየት እድሉ እስካሁን ግልፅ አይደለም።

እህቱ በበኩሏ ልቡ ይገባዋል ብላ እንደማታምን አስረድታለች።

"ቤኔትን እንደ ጀግና እና ፈር ቀዳጅ አድርገው በመንገር ታሪኩን እየጻፉት ነው። ነገር ግን እሱ እንደሚሉት ሰው አይነት አይደለም" ብላለች

"ቀዶ ህክምናውን ያደረጉት ባለሙያዎች ናቸው እንጂ ምስጋና የሚገባቸው እሱ አይደለም" በማለት አስረድታለች።

በጥቃቱ ምክንያት ሹሜከር በዊልቸር ብቻ ተወስኖ የነበረ ሲሆን በአውሮፓውያኑ 2005 በስትሮክ በሽታ ከታመመ ከሁለት አመት በኋላ ህይወቱ አልፏል።

"ወንድሜ ለ19 ዓመታት ተሰቃይቷል፤ መላው ቤተሰብም ተሰቃይቷል" ብላለች።