ናይጄሪያ ለሰባት ወራት ትዊተር ላይ ጥላ የነበረውን እገዳ አነሳች

ታትሟል

ናይጄሪያ ለሰባት ወራት ትዊተር የተሰኘው ማህበራዊ ድር አምባ ላይ ጥላ የቆየችውን እገዳ አንስታለች።

የሃገሪቱ ፕሬዚዳንት ሙሃማዱ ቡሃሪ የክልል ተገንጣዮችን ስለመቅጣት በትዊተር ገጻቸው ያሰፈሩትን መልዕክት ትዊተር ማገዱን ተከትሎ ነው የናይጄሪያ መንግስት ባለፈው ሰኔ ወር ትዊተርን ያገደው።

ባለስልጣናት የማህበራዊ ድር አምባው ለተገንጣዮቹ ወግኗል ሲሉም ከሰዋል።

መንግስት እገዳውን የቀለበሰው ትዊተር ናይጄሪያ ውስጥ ቢሮ መክፈትን ጨምሮ ቅድመ ሁኔታዎችን ለመቀበል ስለተስማማ ነው ብሏል።

በእርምጃው ምክያት በአፍሪካ በሕዝብ ብዛት ቀዳሚ በሆነችው ናይጄሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ማህበራዊ ድር አምባውን በድጋሚ እንዲጠቀሙ ያስችላቸዋል።

አንዳንድ ተጠቃሚዎች ቪፒኤን በመጠቀም ትዊተር መጠቀም ከቀጠሉ በኋላ መንግስት የሚዲያ ድርጅቶችን ጨምሮ ይህን በሚያደርጉት ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ሲዝት ቆይቷል።

ባለፈው ዓመት የናይጄሪያ መንግስት የወሰደው እርምጃ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን አፍኗል በሚል በዓለምአቀፍ ደረጃ ቅሬታን ቀስቅሶበታል።

የማህበራዊ ድር አምባው በሃገሪቱ ለመሥራት መወሰኑ ለናይጄሪያ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ሲል የሃገሪቱ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ልማት ኤጀንሲ አስታውቋል።

ናይጄሪያ እገዳውን በማንሳቷ ውሳኔ ላይ ትዊተር እስካሁን የሰጠው አስተያየት የለም።

"የናይጄሪያን ሃገራዊ ህልውና" ለማዳከም እየተጠቀመበት እና "አመጽን ሊያነሳሱ የሚችሉ የሃሰት ዜናዎችን በማሰራጨት ላይ ነው" በሚል ነበር መንግስት የኢንተርኔት አቅራቢዎች ትዊተርን እንዲያግዱ ያዘዘው።

ከአውሮፓውያኑ 1967 እስከ 1970 የተካሄደውን የናይጄሪያ የእርስ በርስ ጦርነትን በመጥቀስ የፕሬዚዳንት ቡሃሪ "ዛሬ ስነ ምግባር የጎደላቸውን በሚረዱት ቋንቋ እናስተምራቸዋልን" ማለታቸውን ተከትሎ ትዊተር ጽሑፍን ካስወገደ በኋላ ነው እገዳው የመጣው።

ትዊተር በብዙ ናይጄሪያውያን ዘንድ ተወዳጅ ሲሆን ለማስተባበር ሥራም አገልግሏል።

የሰብዓዊ መብት ታጋዮች የፖሊስን ጭካኔ በመቃወም ትዊተርን በመጠቀም ኢንድ ሳርስ በሚል የጀመሩት ዘመቻ የዓለምን ትኩረት ስቦ ነበር።