ከካሜሩን ጋር በሚደረገው የዛሬው ጨዋታ "እስከ መጨረሻው ደቂቃ ድረስ ለመፋለም ዝግጁ ነን"- አሰልጣኝ ውበቱ

ታትሟል

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫ ከአዘጋጇ ካሜሩን ጋር ለምታደርገው ለዛሬው ጨዋታ ቡድኑ ጥሩ ዝግጅት ማድረጉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ገልጸዋል።

በአፍሪካ ውስጥ ስመ ጥር ከሆኑት ቡድኖች የሆነው የካሜሩን ቡድንም ጠንካራና ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች እንደሆኑ እንደሚያውቁ በትናንትናው ዕለት በነበረ ጋዜጣዊ መግለጫ የተናገሩት አሰልጣኝ ውበቱ ሆኖም ቡድናቸው ከዚህ ጨዋታ አንድ ነገር ለማግኘት ዝግጁዎች ነን ብለዋል።

ካሜሩን የዘንድሮው አፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅ በመሆኗ በዛሬው ዕለትም ኢትዮጵያ የምታደርገው ጨዋታ በደጋፊዎቿ ፊት ከምትጫወት ሃገር ጋር ከመሆኑም ቀላል ባይሆንም "ጥቃቅን ስህተቶችን አስወግደን እስከ መጨረሻው ደቂቃ ድረስ ለመፋለም ዝግጁ ነን።" ይላሉ አሰልጣኙ

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫ መክፈቻ በነበራት ጨዋታ በኬፕቨርዴ አንድ ለምንም ተረታለች።

በዚህ ጨዋታ አንድ ተጫዋች በቀይ ካርድ በመውጣቱ አብዛኛውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በአንድ ሰው ጎዶሎ እንደተጫወቱም የጠቀሱት አሰልጣኙ ይህም በዋልያዎቹ ላይ ተፅእኖ ፈጥሯል ብለዋል።

"ይህ በተጨዋቾቻችን በአካልና በመንፈስ ጠንካራ እንዳይሆኑ ያደረገ ክስተት ነበር።" ያሉት አሰልጣኝ ውበቱ አክለውም ቡድኑ በጥሩ አቋም ላይ አለ ብለዋል።

"ቢሆንም አሁን ወደ አቋማችን ተመልሰናል። ይህንንም በልምምድ ሜዳና በካምፕ ማየት ችለናል። ከዛሬው ጨዋታ የተሻለ ነገር እንደምናገኝ ተስፋ አለኝ።" በማለት አስረድተዋል።

ውበቱ አክለው በካሜሩን ጋር በሚኖራቸው ጨዋታ ብሔራዊ ቡድኑ የሚታወቅበትን ጨዋታ ለማሳየት እንደሚሞክሩ ጠቁመዋል።

የመጀመሪያው ጨዋታ ለቡድናቸው ፈታኝ እንደነበር ጠቁመው የተሸነፈውም በአንድ ጎል ነው ይላሉ።

ቡድናቸው ጎል የተቆጠረበት በመጀመሪያ አጋማሽ መገባደጃ ላይ መሆኑንም ጠቅሰው "ይህ የሆነው በትኩረት ማነስ ሊሆን ይችላል።" ብለዋል።

ለዚህም እንደ ማስረጃ የሚያቀርቡት ኢትዮጵያ ያደረገቻቸውን ያለፉትን ስድስ ሰባት ጨዋታዎችን በመጥቀስ ነው።

"ያለፉትን ስድስት ሰባት የኢትዮጵያ ጨዋታዎች ብንመለከት ኳስን በመቆጣጠር ከተጋጣሚዎቻችን የተሻልን ነበርን። ጋናን ብናነሳ፣ ደቡብ አፍሪካ አሊያም ዚምባብዌ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ነበረን።" ይላሉ።

በመጀመሪያው ጨዋታ ያሬድ ባየህ ቀይ ካርድ ከተመለከተ በኋላ ተቀይሮ የወጣው አማካዩ መሱድ ሞሐመድ ካሜሩንን ብናከብራትም ውጤት ለማግኘት መፋለማችን ግን አይቀርም ብሏል።

"ካሜሩን ጠንካራ ቡድን እንደሆነች እናውቃለን። አፍሪካን ወክላ በዓለም ዋንጫ ስትጫወት እኛ ኢትዮጵያዊያን ስንደግፋት ነበር። አልፎም የሳሙዔል ኤቶ ሃገር በመሆኗ ክብር እንሰጣታለን። ነገር ግን ዛሬ ከፈጣሪ ጋር ጥሩ ፍልሚያ እንደምናደርግ አስባለሁ።" ብሏል መሱድ በትናንትናው ዕለት በነበረ ጋዜጣዊ መግለጫ

ከቡድኑ አባላት በኮቪድ ምክንያት አሊያም በጉዳት የማይሰለፍ አለ ወይ ተብለው የተጠየቁት አሠልጣኙ ኮቪድን በተለመከተ ተጫዋቾችን ጨምሮ ሁሉም የብሔራዊ ቡድኑ አባላት ከኮቪድ-19 ነፃ መሆናቸውን ተናግረዋል። "ይህ ለኛ መልካም ዜና ነው" ብለዋል

ጉዳትን በተመለከተ ለግብፅ ሊግ የሚጨዋተውና ልምድ አላቸው ከሚባሉት ተጫዋቾች አንዱ ሽመልስ በቀለ በጉዳት ምክንያት እንደማይሰለፍ ተናግረዋል። ከሃገር ውጭ ከሚጫወቱት ሁለት ተጫዋቾች አንዱ የሆነው ሽመልስ ከትናንት በስቲያ ጉዳት እንዳጋጠመው አሰልጣኝ ውበቱ ገልጸዋል።

"ከሃገር ውጭ ከሚጫወቱ ሁሉት ተጫዎቾቻችን አንዱ ነው። ቢሆንም ልምዱን ልንጠቀምበት አልቻልንም። ከትናንት በስቲያ እንደገና ጉዳት አጋጥሞታል። ከሱ በቀር ሁሉም ተጫዋቾቻችን ለዛሬው ፍልሚያ ዝግጁ ናቸው።" ብለዋል።