ኮቪድ፡ ግማሽ አውሮፓ በሳምንታት ውስጥ በኦሚክሮን ይያዛል- የዓለም ጤና ድርጅት

ታትሟል

በሚቀጥሉት ስድስት እና ስምንት ሳምንታት ውስጥ ግማሽ አውሮፓ ኦሚክሮን በተሰኘው የኮቪድ ዝርያ እንደሚያዝ የዓለም ጤና ድርጅት አስጠነቀቀ።

ዶ/ር ሃንስ ክሉጅ የዴልታ ዝርያ ካሳየው ከፍተኛ ጭማሪ በላይ ኦሚክሮን "ከምዕራብ ወደ ምስራቅ እየተዛመተ ያለው ማዕበል" አካባቢውን እያጥለቀለቀ ነው ብለዋል።

ትንበያው በ2022 የመጀመሪያ ሳምንት በመላው አውሮፓ ሰባት ሚሊዮን ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ላይ የተመሠረተ ነው።

የቫይረሱ ስርጭት በሁለት ሳምንት ውስጥ ከእጥፍ በላይ ጨምሯል።

"አገራት ዴልታን እስከ 2021 መገባደጃ ድረስ ለመከላከል እያደረጉ ያለው ጥረት ላይ የኦሚክሮን ዝርያ ከምዕራብ ወደ ምስራቅ እንደማዕበል አካባቢውን እየጠራረገ ነው" ሲሉ ዶ/ር ክሉጅ ለመገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።

መቀመጫውን ሲያትል ያደረገውን የጤና መለኪያዎች እና ግምገማ ኢንስቲትዩትን ጠቅሰው "በቀጣዮቹ ስድስት እና ስምንት ሳምንታት ውስጥ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነው የአውሮፓ ሕዝብ በኦሚክሮን ይያዛል" ሲሉ ትንበያቸውን ሰጥተዋል።

የአውሮፓና የመካከለኛው እስያ አገሮች "ከፍተኛ ጫና ውስጥ መሆናቸውን" ጠቅሰው ቫይረሱ ከምዕራባውያን አገሮች ወደ ባልካን መዛመቱን ተናግረዋል።

አክለውም "እያንዳንዱ አገር የሚሰጠው ምላሽ በጤና ተቋማት ሁኔታ፣ ባለው ሀብቶች ፣ በክትባት አወሳሰድ፣ በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አውድ ይወሰናል" ብለዋል።

የቅርብ ጊዜ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ኦሚክሮን ከቀደሙት የኮቪድ ዝርያዎች ያነሰ ለህመም ይዳርጋል። ሆኖም ኦሚክሮን በጣም ተላላፊ ከመሆኑ ባለፈ ሙሉ በሙሉ የተከተቡ ሰዎችን ጭምር ሊይዝ ይችላል።

በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑም የጤና ተቋማት ላይ ከባድ ጫና ፈጥሯል።

ሰኞ ዕለት ዩናይትድ ኪንግደም 142 ሺህ 224 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ሪፖርት ስታደርግ 77 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል።

በሌሎች አገራትም ሆስፒታል የሚገቡ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው። የፈረንሣይ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ኦሊቪዬ ቬራ ባለፈው ሳምንት እንደገለጹት ጥር ወር ለሆስፒታሎች ከባድ እንደሚሆን አስጠንቅቀዋል።

ዴልታ በአይሲዩ ክፍሎች ላይ ጫና እያሳደረ ባለበት ወቅት ኦሚክሮን የሆስፒታሎችን "መደበኛ" አልጋዎችን እየተቀራመተ መሆኑን አክለዋል።

ፖላንድ ወረርሽኙ ከጀመረ ወዲህ 100 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ መሞታቸውን አስታውቃለች። ፖላንድ በኮቪድ-19 ምክንያት ሕይወታቸውን ባጡ ሰዎች ቁጥር ከዓለም ስድስተኛ ደረጃን የያዘች ሲሆን 40 በመቶ የሚሆነው ሕዝቧ ያልተከተበ ነው።

አና ፖፖቫ የተባሉት የሩሲያ ከፍተኛ የጤና ባለሙያ ለመንግሥት የኮሮናቫይረስ ግብረ ኃይል እንደተናገሩት የቫይረሱን ሥርጭት ለመቆጣጠር እርምጃ ካልተወሰደ በየዕለቱ በኮቪድ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር 100 ሺህ ሊደርስ ይችላል።

በየዕለቱ የሚመዘገው በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በኅዳር መጀመሪያ ላይ ከተመዘገበው 41 ሺህ 335 በከፍተኛ ደረጃ ላይ እየቀነሰ ነበር ሲል ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ፖፖቫ እንዳሉት እስካሁን በ13 የአገሪቱ ክልሎች 305 በኦሚክሮን ዝርያ የተያዙ ሰዎች ተገኝተዋል። ሩሲያ እስካሁን 311 ሺህ 281 ሞት እና 10.5 ሚሊዮን ደግሞ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን መዝግባለች።

የፋርማሲዩቲካል ተቋሙ ፋይዘር ሰኞ እለት እንዳስታወቀው በመጋቢት ወር ከኦሚክሮን ዝርያ የሚከላከለውን ክትባቱን ማምረት ሊጀመር እንደሚችል ተናግሯል። የጤና ባለሙያዎች ግን አስፈላጊ ስለመሆን አለመሆኑ እስካሁን ግልጽ አይደለም ብለዋል።