ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን መልቀቅ በኋላም በሱዳን የተቃውሞ ሰልፎች ቀጥለዋል

ተቃዋሚ ሰልፈኞች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በሱዳን ወታደራዊው መንግሥት ሥልጣኑን ለሲቪል አስተዳደር እንዲያስረክብ የሚጠይቁ ሰልፎች ቀጥለዋል።

የፀጥታ ኃይሎች በበኩላቸው በዲሞክራሲ ጠያቂ ሰልፈኞች ላይ አስለቃሽ ጭስ ተኩሰዋል።

አስለቃሽ ጭስ ሲተኮስባቸው የነበሩ ሰልፈኞች በዋና ከተማዋ ካርቱምና በወደብ ከተማዋ በፖርት ሱዳን አካባቢ አደባባይ የወጡ ናቸው።

የትናንቱ ሰልፍ በሱዳን መንግሥት ውስጥ የሲቪል አስተዳደርን ይወክሉ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዶክ ሥልጣን መልቀቃቸውን ተከትሎ የተደረገ ነው።

ሐምዶክ ሥልጣን የለቀቁት ከወታደራዊው አስተዳደር ጋር የደረሱት ሥልጣን የመጋራቱ ሐሳብ ቁጣ መቀስቀሱን ተከትሎ ነው።

ባለፈው ጥቅምት አጋማሽ ላይ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት መደረጉን ተከትሎ የሲቪል አስተዳደር የአገሪቱን ሥልጣን እንዲይዝ የሚጠይቁ አያሌ ሰልፎች በመላዋ ሱዳን ሲደረጉ ቆይተዋል።

ሆኖም ለዚህ የሕዝብ ጥያቄ የፀጥታ ኃይሎች ኃይል የተቀላቀለበት ምላሽ ሲሰጡ ሰንብተዋል።

ሲካሄዱ በቆዩት ተቃውሞዎች 56 ሰልፈኞች መገደላቸውን የሱዳን የሐኪሞች ኮሚቴ ይፋ አድርጓል። አብዛኞቹ የተገደሉትም ከፀጥታ ኃይሎች በተተኮሰ ጥይት ነው ብሏል።

በትናንቱ ተቃውሞ ሰልፈኞች ጎማ በማቃጠል፣ መንገድ በድንጋይ ክምር በመዝጋት ጭምር ቁጣቸውን የገለጹ ሲሆን ይህም በካርቱምና በኡምዱርማን ከተሞች የታየ ነው።

በወደብ ከተማዋ በፖርት ሱዳን ደግሞ በርካታ ቁጥር ያለው ተቃዋሚ አደባባይ በመውጣቱ የተኩስ ድምጽ በተደጋጋሚ ይሰማ ነበር ተብሏል።

ከጥቂት ወራት በፊት የተካሄደው መፈንቅለ መንግሥት መሪ የሚባሉት ጄኔራል አብደል ፋታህ አልቡርሐን የወታደሮቹን እርምጃ ደግፈዋል። "ወታደሮቼ የእርስ በእርስ ጦርነት እንዳይቀሰቀስ ማድረግ ያለባቸውን ነው ያደረጉት" ሲሉ ተሰምተዋል።

ጨምረው እንዳሉትም ሱዳን ወደ ሲቪል አስተዳደር የመጓዝ ሂደቷን አልቀለበሰችም፤ ምርጫም በሐምሌ 2023 ለማድረግ የተያዘው ዕቅድ እንዳለ ነው።

ሰኞ ዕለት አልቡርሐን ለወታደራዊ አመራሮች እንደተናገሩት የአገሪቱ ደኅንነት ያለው በወታደሩ እጅ ነው።

ዲሞክራሲያዊ ሽግግር መካሄድ ሚችለውም ወታደሩ አገሪቱን ሰላማዊነት ሲያስጠብቅ ነው።

የዲሞክራሲ አቀንቃኝ ሱዳናዊያን ግን የወታደሩ ክንፍ የሕዝብን አብዮት ሰርቋል ሲሉ ይከሳሉ።

ለረዥም ዓመታት ሱዳንን በፈርጣማ ክንዳቸው ሲመሩ የቆዩት ኦመር አልበሽር በሕዝብ ተቃውሞ ከሥልጣናቸው የተነሱት ከሦስት ዓመት በፊት ነበር።