የሊቀ ጳጳስ ዴዝሞንድ ቱቱ አስክሬን በውሃ እንደሚሟሟ ተገለጸ

የሊቀ ጳጳስ ዴዝሞንድ አስክሬን በኬፕ ታውን በሚገኘው ቅዱስ ጊዎርጊስ ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን ተቀምጦ በሺዎች የሚቆጠሩ ደቡብ አፍሪካውያን እየተሰናበቱ ነው።

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, የሊቀ ጳጳስ ዴዝሞንድ አስክሬን በኬፕ ታውን በሚገኘው ቅዱስ ጊዎርጊስ ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን ተቀምጦ በሺዎች የሚቆጠሩ ደቡብ አፍሪካውያን እየተሰናበቱ ነው።
ታትሟል

የፀረ አፓርታይድ ታጋዩ ሊቀ ጳጳስ ዴዝሞንድ ቱቱ አስክሬን በውሃ እንዲሟሟ ሊደረግ ነው።

የነጻነት ትግል ቁንጮው ሊቀ ጳጳስ ዴዝሞንድ ከባቢ አየርን በማይጎዳ ሁኔታ አስክሬናቸው በውሃ እንዲሟሟ እንደሚደረግ ተገልጿል።

ሬቨረንድ ማይክል ዊደር "ዴዝሞንድ የአካባቢ መብት ተቆርቋሪ ነበሩ። አስክሬናቸው በውሃ እንዲሟሟ ተናዘዋል" ብለዋል።

የነጻነት ታጋዩ አስክሬን በውሃ የሚሟሟበት ሂደት አኳሜሽን (Aquamation) ተብሎ ይጠራል።

የሊቀ ጳጳስ ዴዝሞንድ አስክሬን በኬፕ ታውን በሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል ውስጥ ተቀምጦ በሺዎች የሚቆጠሩ ደቡብ አፍሪካውያን እየተሰናበቱት ነው።

ሊቀ ጳጳሱ በ90 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ባለፈው ሳምንት ነበር።

ዋሊ ምዱሊ የተባለ ግለሰብ ከ1,000 ኪሎ ሜትር በላይ ተጉዞ ነው ሊቀ ጳጳሱን የተሰናበተው።

ወደ ኬፕ ታውን ላደረገው ጉዞ ቤተሰቦቹና ጓደኞቹ በገንዘብ ረድተውታል።

መንገድ ላይ ሳለ በነዳጅ ማደያ እያደረም ነበር የነጻነት ታጋዩን ለመሰናበት ኬፕ ታውን የደረሰው።

"አስክሬናቸውን አይቼ መሰናበቴ እጅግ አስደስቶኛል። መንፈሳቸው ከእኔ ጋር እንዳለ ይሰማኛል" ብሏል ለቢቢሲ።

"የእሳቸውን ትውስታ እስከ ሕይወቴ ፍጻሜ ይዤው እኖራለሁ" ያለው ዋሊ፤ መላው ደቡብ አፍሪካውያን በሊቀ ጳጳስ ዴዝሞንድ አስተምህሮት ቢኖር መልካም ነው ሲልም ምክሩን ለግሷል።

የሊቀ ጳጳሱ የመጨረሻው ሥርዓተ ቀብርና የስንብት ሥነ ሥርዓት በቀጣይ ሳምንት ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።

ይህም በቤተሰቦቻቸው ብቻ በሚገኙበት የሚካሄድ ወይም ሕዝባዊ ስለመሆኑ እስካሁን አልታወቀም።

ከመሞታቸው በፊት በተናዘዙት መሠረት "ቅንጡ የቀብር ሥነ ሥርዓት" አይፈልጉም። አስከሬናቸው በጣም ርካሽ በሆነ ሬሳ ሳጥን እንዲቆይ እና በሬሳ ሳጥናቸው ላይ የሚቀመጠው አበባ ከቤተ ክርስቲያን የተገኘ እንዲሆን ተናዘዋል።

የአስክሬናቸው ቅሪትም በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ይቀበራል።

ዴዝሞን ቱቱ በቤተ ክርስቲያኑ ለ35 ዓመታት ያህል ሊቀ ጳጳስ ሆነው አገልግለዋል።

አስክሬን በውሃ የሚሟሟው እንዴት ነው?

አኳሜሽን የሚባለው ሂደት የሚከናወነው የአንድን ሰው አስክሬን በውሃ እና ሀይድሮክሳይድ ውህድ ውስጥ በማሟሟት ነው።

መጀመሪያ የግለሰቡ አስክሬን ይመዘናል። ከዚያም የውሃ እና ሀይድሮክሳይድ ውህዱ በ150 ሴንቲ ግሬድ እንዲፈላ ይደረጋል። ከዚያም አስክሬኑ ይሟሟል።

ይህ ሂደት ሳይንሳዊ መጠሪያው አልካሊን ሀይድሮሊስስ (alkaline hydrolysis) ይባላል።

ለ90 ደቂቃ ያህል አስክሬኑ ከቆየ በኋላ የግለሰቡ ሰውነት ሲሟሟ፣ አጥንቱ ይቀራል።

የሟሟውን አስክሬን ለማድረቅ 120 ሴንቲ ግሬድ ሙቀት ይለቀቃል።

የግለሰቡ አስክሬን በዚህ መንገድ ሟምቶ አመድ ከወጣው በኋላ አስክሬኑን መቅበር ወይም በሟች ኑዛዜ መሠረት በሚመርጡት አካባቢ መበተንም ይቻላል።

የሰውን አስክሬን በእሳት ከማቃጠል በተቃራኒው ይህ መንገድ ከባቢ አየርን አይጎዳም።

ሬሳ ሲቃጠል የሚወጣውን በካይ ካርቦን ዳይኦክሳይድ 90 በመቶ ይቀንሳል።