የኢትዮጵያ የካቶሊክ ቀሳውስት ኮንፍረንስ ለጦርነቱ ተጎጂዎች 2 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያሰባስብ አስታወቀ

የኢትዮጵያ የካቶሊክ ቀሳውስት ኮንፍረንስ ከሰሞኑ በሞጆ ከተማ በሚገኘው ማዕከል ያካሄደው ጉባኤ ዋነኛ ትኩረት የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት እንደነበረ ተገልጿል።

የፎቶው ባለመብት, Vatican News

የምስሉ መግለጫ, የኢትዮጵያ የካቶሊክ ቀሳውስት ኮንፍረንስ ከሰሞኑ ያካሄደው ጉባኤ ዋነኛ ትኩረት የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት እንደነበረ ተገልጿል።
ታትሟል

የኢትዮጵያ የካቶሊክ ቀሳውስት ኮንፍረንስ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ለተጎዱ ወገኖች መደገፊያ የሚውል ሁለት ሚሊዮን ዶላር እንደሚያሰባስብ ይፋ አደረገ።

ዘ ካቶሊክ ቢሾፕስ ኮንፍረንስ ኦፍ ኢትዮጵያ ወይም ሲቢሲኢ ገንዘቡን ከአጋር አብያተ ክርስቲያናት፣ ከካቶሊክ ተቋማት እንዲሁም ከእምነቱ ተከታዮች ለመሰብሰብ ማቀዱን ገልጿል።

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ድምጽ በሆነው 'ቫቲካን ኒውስ' ድረ ገጽ ያወጣው መግለጫ እንደሚጠቁመው፤ የሚሰበሰበው ገንዘብ በጦርነቱ ሳቢያ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችን ለመርዳት ይውላል።

የኢትዮጵያ የካቶሊክ ቀሳውስት ኮንፍረንስ ከሰሞኑ በሞጆ ከተማ በሚገኘው ማዕከል ያካሄደው ጉባኤ ዋነኛ ትኩረት የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት እንደነበረ ተገልጿል።

በጎርጎሮሳውያኑ ካላንደር የገና በዓል ባለፈው ቅዳሜ ሲከበር የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መሪ አቡነ ፍራንሲስ በመላው ዓለም ሰብአዊ ቀውስ እያስከተሉ ያሉ ጦርነቶች እንዲገቱ ጥሪ አድርገዋል።

የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ከተነሳ ወዲህ አቡነ ፍራንሲስ እንዲሁም የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያንም በተለያዩ ጊዜያት ግጭቱ እንዲያበቃ ጠይቀዋል።

ቫቲካን ኒውስ እንደዘገበው፤ ሁሉም ወገኖች ወደ ድርድር እንዲመጡ ቀሳውስቱ ጠይቀዋል።

"ጦርነት አውዳሚ ነው። ሕይወትና ንብረት ያጠፋል። ማኅበረሰብን ይከፋፍላል። የኢትዮጵያ ጦርነት እያስከተለ ያለውን ሰብአዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ እና ማኅበራዊ ቀውስ እያየን ነው" ብለዋል ቀሳውስቱ።

በጦርነቱ ሳቢያ በርካቶች ሕይወታቸውን ማጣታቸው፣ ሴቶች መደፈራቸው፣ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸው፣ ማኅበራዊ ትስስሩ መፍረሱ እና ለእስር የተዳረጉም መኖራቸው እንደሚያሳዝን አክለዋል።

በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በደረሰው ቀውስ ሳቢያ የነገ ሕይወታቸው መጨለሙ ልብ የሚሰብር ነው ሲሉም ቀሳውስቱ ተናግረዋል።

"ለኢትዮጵያ እየፀለይን ነው" ያሉት ቀሳውስቱ "ለአገሪቱ፣ በዜጎች እጣ ፈንታ ለሚወስኑት መሪዎች፣ ለዜጎች፣ ለተራቡት፣ ለተፈናቀሉት እና ለታሰሩት ፀሎት ያሻል" ብለዋል።

በአገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑ ወገኖች ወደ ድርድር ጠረጴዛ እንዲመጡ እንዲሁም ማኅበራዊ ትስስሩ እንዲመለስም ቤተ ክርስቲያንን ጨምሮ ሁሉም ዜጋ የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።

ሁለት ሚሊዮን ዶላር (100,000,000 ብር ገደማ) ከማሰባሰብ በተጨማሪ በሌሎችም መንገዶች በጦርነቱ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ መስጠት እንደሚቀጥሉም አክለዋል።

የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ሆኑት አቡነ ፍራንሲስ በሰሜን ኢትዮጵያ አየተካሄደ ያለውን ጦርነት በተለያዩ አጣሚዎች በማንሳት ሰላም እንዲወርድ ጥሪ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።

አንድ ዓመት ባለፈው በዚህ ጦርነት ወደ አስር ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ሰብአዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የገለጸ ሲሆን፣ ለዚህም የገንዘብ እጥረት እንዳጋጠመው መሳወቁ ይታወሳል።