በአማራ ክልል ተጥሎ በነበረው የሰዓት እላፊ ገደብ ላይ ማሻሻያ ተደረገ

ታትሟል

በአማራ ክልል ተጥሎ በነበረው የሰዓት እላፊ ገደብ ላይ ማሻሻያ መደረጉን የክልሉ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አስታወቁ።

አቶ ግዛቸው ሙሉነህ በክልሉ ውስጥ ሲካሄድ የነበረውን ጦርነት ተከትሎ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ላይ ለደኅንነት ሲባል ተጥሎ የነበረው የሰዓት እላፊ ገደብ ላይ ለውጥ መደረጉን አመልክተዋል።

የክልሉ ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊው ዛሬ ሐሙስ ታኅሣሥ 14/2014 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት የአማራ ክልል የፀጥታ ኮማንድ ፖስት በክልሉ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ከገመገመ በኋላ ነው ተጥሎ በነበረው የሰዓት እላፊ ገደብ ላይ ማሻሻያ ያደረገው።

የፀጥታ ኮማንድ ፖስቱ በክልሉ ያለው የፀጥታ ሁኔታ እየተሻሻለ መምጣቱን በመገምገም የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴዎች እንዳይዳከሙ እንዲሁም በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ ከውጭ አገራት የሚመጡ ዜጎችን ታሳቢ በማድረግ የሰዓት እላፊ ገደቡ ላይ ለውጥ ተደርጓል።

በዚህም መሠረት ተግባራዊ ሲደረግ የነበረውና ከምሽቱ 2 ሰዓት እስከ ንጋት 12 ሰዓት ተጥሎ የቆየው የሰዓት እላፊ ገደብ ከምሽቱ 4 ሰዓት እስከ ንጋት 11 ሰዓት ድረስ እንዲሆን ለውጥ መደረጉን አቶ ግዛቸው አስታውቀዋል።

የህወሓት ኃይሎች ከትግራይ ክልል ጋር በሚዋሰኑ የአማራ ክልል አካባቢዎች ላይ ጥቃት ከፍተው በርካታ ቦታዎችን መያዝ በጀመሩበት ጊዜ ነበር ለፀጥታ ቁጥጥር ሲል ክልሉ የሰዓት እላፊ ገደብ የጣለው።

በአሁኑ ጊዜ ቀደም ሲል በህወሓት ተይዘው የነበሩ የአማራ ክልል አካባቢዎች በፌደራልና በክልሉ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ከመግባታቸው በተጨማሪ የአማጺያኑ እንቅስቃሴ መገታቱ ይታወቃል።

በተለይ በከተሞች አካባቢ ጥብቅ ሆኖ የቆየው የሰዓት እላፊ ገደብ በሰዎች እና በተለያዩ ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ተጽእኖን አስከትሎ እንደነበር ይታመናል።

በአሁኑ ጊዜ በክልሉ ውስጥ የነበረው የፀጥታ ስጋት በአብዛኛው በመቀረፉ የሰዓት እላፊ ገደቡ ላይ ለውጥ መደረጉን የአማራ ክልል የፀጥታ ኮማንድ ፖስት አመልክቷል።

ጦርነቱ ተስፋፍቶ የህወሓት ኃይሎች በርካታ የአማራ ክልል ከተሞችን መያዛቸውን ተከትሎ የክልሉ ምክር ቤት አማጺያኑን ለመመከት ለሕዝቡ አስቸኳይ ጥሪ ባስተላለፈበት ወቅት ነበር በሁሉም የክልሉ ከተሞች ተፈጻሚ የሚሆን ሰዓት እላፊ የደነገገው።

በዚህም መሠረት የክልሉ ምክር ቤት ፍቃድ ከሚሰጣቸው ተቋማት ውጪ በሁሉም ከተሞች ከምሽቱ 2፡00 በኋላ እንቅስቃሴ ማድረግ አይቻልም ተብሎ ክልከላ ተጥሎ ነበር።