ጳጳስ ፍራንሲስ ሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃትን ሰይጣናዊ ድርጊት ሲሉ አወገዙ

የካቶሊክ ቤተክርስቲያን መሪ ጳጳስ ፍራንሲስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የካቶሊክ ቤተክርስቲያን መሪ ጳጳስ ፍራንሲስ
ታትሟል

የካቶሊክ ቤተክርስቲያን መሪ ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ሴቶች ላይ የሚደርስ የቤት ውስጥ ጥቃትን "ሰይጣናዊ ድርጊት" ሲሉ አወገዙ።

የሴቶች ጥቃትን በተመለከተ ከዚህ ቀደም ካደረጓቸው ንግግሮች ይህኛው ጠንካራው ነው ተብሏል።

ትላንት በተካሄደ የቤተክርስቲያኒቱ አገልግሎት ላይ ነበር ጳጳሱ ንግግሩን ያደረጉት። በጣልያኑ ቲጂ5 የቴሌቭዥን ጣቢያም ተላልፏል።

ጳጳሱ ንግግሩን ሲያደጉ በስፍራው ከነበሩት መካከል ወሲባዊ ጥቃት ደርሶባት የነበረች ሴት ትጠቀሳለች።

"በየቤታቸው የሚደበደቡ እና ጥቃት የሚደርስባቸው ሴቶች እጅግ በርካታ፣ በርካታ ናቸው" ብለዋል ጳጳሱ።

አያይዘውም "እራሳቸውን መከላከል የማይችሉ ሰዎች ላይ የሚደርስ ጥቃት ሰይጣናዊ ድርጊት ነው። ሴቶቹ የሚሰነዘርባቸውን ቡጢ ለመከላከል ከመሞከር ውጪ አማራጭ የላቸውም" ሲሉ የሴቶች ጥቃትን ኮንነዋል።

የቤት ውስጥ ጥቃትን "እጅግ በጣም አሳፋሪ ነው" በማለት ጳጳሱ አውግዘውታል።

ጂኦቫና የተባለች ከአራት ልጇቿ ጋር ከአጋሯ ጥቃት ያመለጠች ሴት ጳጳሱ ንግግር ሲያደርጉ ታዳሚ ነበረች።

"አንቺ የተከበርሽ ሴት ነሽ። እዚህ የተገኘሽውም የተከበርሽ ስለሆንሽ ነው። ድንግል ማርያምን ተመልከችና ብርታት አግኚ" ሲሉ ጳጳሱ ከጂኦቫና ጋር ተነጋግረዋል።

አንዲት ሴት ጥቃት ቢደርስባትም የማንነት ክብሯ እንደማይነካም ተናግረዋል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽ መሰራጨት ከጀመረ ወዲህ ጳጳሱ የቤት ውስጥ ጥቃትን በማውግዝ በተደጋጋሚ ንግግር አድርገዋል።

በርካታ ሴቶች በወረርሽኙ ምክንያት ቤት ውስጥ ጥቃት ከሚያደርሱባቸው አጋሮች ጋር ዘለግ ያለ ጊዜ ለመቆየት ተገደዋል። ይህም የቤት ውስጥ ጥቃት ቁጥርን አንሯል።

የተባበሩት መንግሥታት 13 አገራትን በተመለከተ ባወጣው ሪፖርት መሠረት፤ በዳሰሳው ከተካተቱ ሴቶች ከፊሉ ወረርሽኙ መነሳቱን ተከትሎ አንዳች ዓይነት ጥቃት ደርሶባቸዋል።

የጣልያን ፖሊስ ባለፈው ወር ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት፤ በየቀኑ በ90 አጋጣሚዎች ሴቶች ላይ ጥቃት ደርሷል። 62 በመቶ ያህሉ የቤት ውስጥ ጥቃት ነው።

ከጂኦቫና ጋር የተነጋገሩት ጳጳስ ፍራንሲስ፤ ተስፋ እንዳትቆርጥ አበረታተዋታል።

ጨምረውም "የጽናት ምልክት ነሽ። ጽናትሽ ለብዙዎች ምሳሌ ይሆናል። ከቀደመው ጊዜ የተሻለ ሕይወት ይጠብቅሻል" ብለዋታል።