ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ናይጄሪያዊቷ ወታደር የደንብ ልብስ እንደለበሰች የታገቢኛለሽ ጥያቄን በመቀበሏ ታሰረች
አንዲት ሴት ወታደር ናይጄሪያ ውስጥ በሥራ ላይ እያለች የታገቢኛለሽ ጥያቄን መቀበሏን ተከትሎ በቁጥጥር ስር ውላለች ሲሉ የጦሩ ቃለ አቀባይ ተናግረዋል።
"የወታደራዊ የደንብ ልብሷን እንደለበሰች በፍቅር ግንኙነት ሁኔታ በመታየቷ ወታደራዊውን የሥነ ምግባር ደንብ ጥሳለች" ሲሉ ቃል አቀባዩ አክለዋል።
ከወታደሯ ፊት ለፊት የተንበረከከና ቀለበት የያዘ ግለሰብ 'ታገቢኛለሽ?' ብሎ ሲጠይቅና እሷም በእሺታ ተቀብላ ቀለበቱን ሲያጠልቅላት የሚያሳይ ቪዲዮ ባለፈው ሳምንት ወጥቶ ነበር።
በአካባቢው የነበሩ ተመልካቾችም በደስታ ሲያጨበጭቡም ቪዲዮው ያሳያል።
አንድ የሴቶች መብት ተሟጋች ድርጅት ጦሩ በወታደሯ ላይ አድልዎ ፈፅሟል ሲሉ ከሰዋል።
"ሙሉ ወታደራዊ መለዮ በለበሱና በተመሳሳይ በአደባባይ ላይ የፍቅር ግንኙነታቸውን በገለጹ ወንድ ወታደሮች ላይ ተመሳሳይ እርምጃ አልተወሰደም" ሲሉ በሴቶች ማጎልበት የሚሰራውና የሕግ ድጋፍ ቡድን የሚሰጥ አንድ ድርጅት ገልጿል።
የሰብአዊ መብት ተሟጋች እና የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንታዊ ዕጩ ኦሞዬሌ ሶዎር የሠራዊቱን ውሳኔ "ፆተኛ" ሲሉ አውግዘውታል።
ወታደሯ በመንግሥት የወጣቶች ማሰልጠኛ መርሃ ግብር፣ ብሔራዊ የወጣቶች አገልግሎት በመባል እየሰለጠነ ከነበረ አንድ ወጣት የቀረበላት እንጋባ ጥያቄውን ተቀብላለች።
በዚህ መርሃ ግብር መሰረት ከዩኒቨርሲቲዎች እና ከሌሎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተመረቁ ተማሪዎች አንድ ዓመት የሚፈጅ አስገዳጅ ትምህርት ከሠራዊቱ ያገኛሉ።
የጋብቻ ጥያቄው የቀረበው በምዕራብ ኳራ ግዛት በስልጠና ፕሮግራም ወቅት ሲሆን መቼ እንደነበረም ግልፅ አይደለም። ነገር ግን ቪዲዮው የወጣው ባለፈው ሳምንት ነበር።
ብዙ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ጥንዶቹን እንኳን ደስ አላችሁ በማለት ግለሰቡ የእንጋባ ጥያቄውን በማቅረቡ ያሞካሹትን ያህል ሌሎች ደግሞ ተሳልቀውበታል።
የጦር ኃይሉ ቃል አቀባይ ጄኔራል ክሌመንት ንዋቹኩ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ወታደሯ የሠራዊቱን የሥነ ምግባር መመሪያ እንዲሁም የማኅበራዊ ሚዲያ ፖሊሲውን ጥሳለች።
"ምግባሯ መልካም ሥርዓት የጎደለው ወታደራዊ ዲሲፕሊኑን የጎዳ ነው" ብለዋል።
ጄኔራል ክሌመንት ንዋቹኩ አክለውም "የአሰልጣኞቹ ተግባር የወጣቶችን ቡድን አባላት ማሰልጠን እንጂ ከማንኛውም ሰልጣኝ ጋር ያልተገባ ግንኙነት መፍጠር አይደለም" ብለዋል።
የአገሪቱ ብሔራዊ የወጣቶች አግልግሎት እስካሁን በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት አልሰጠም።