የፈረንሳይ ዜጎች በማዳጋስካር መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተፈረደባቸው

ፕሬዝዳንት አንድሪ ራጆኤሊና

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በማዳጋስካር ፕሬዝዳንት አንድሪ ራጆኤሊና ላይ መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግ በማቀድ ሁለት የፈረንሳይ ዜጎች የ10 እና 20 አመት እስር ተፈርዶባቸዋል።

ፖል ራፋኖሃራና እና ፊሊፕ ፍራንኮይስ የተባሉት ግለሰቦች የመንግስትን ደህንነት አደጋ ላይ በመጣል፣ ፕሬዚዳንቱን ለመግደር በማሴርና የወንጀል ማህበር በመፍጠር በሚል ተከሰው ነበር።

ሌሎች 20 ተከሳሾችም በእስር ተቀጥተዋል።

የግለሰቦቹ ጠበቃ ቅጣቱን በመቃወም ይግባኝ ለማቅረብ ማቀዱን ተናግሯል።

"እኔ እንደጠበቅኩት ሳይሆን ፍትሃዊ ያልሆነ ፍርድ ነው...የፖለቲካ ክስ ነው" ሲሉ ጠበቃ ሶሎ ራድሰን መናገራቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ባለሥልጣናቱ እንዳሉት በሐምሌ ወር በግለሰቦቹ ላይ ባደረጉት ብርበራ ማስረጃ የሚሆኑ "ኢሜይሎችን ፣መሳሪያዎችን እና ገንዘቦችን ከያዙ በኋላ "አፖሎ 21" የተሰኘውን የመፈንቅለ መንግሥት ሴራ ማግኘታቸውን ተናግረዋል ።

በመረጃውም መሰረት ፕሬዝዳንቱን ጨምሮ በርካታ ሰዎችን "የማጥፋት እና የማስወገድ" ዕቅዶችን እንዳካተተም ተናግረዋል።

ፊሊፕ ፍራንኮይስ የተባለው የፈረንሳይ ጦር የቀድሞ ኮሎኔል በ10 አመት እስራት ተቀጥቷል።

በአንድ ወቅት የፕሬዚዳንት ራጆኤሊና አማካሪ ሆኖ ያገለገለውና የፈረንሳይና የማዳጋስካር ጥምር ዜግነት ያለው ፖል ራፋኖሃራና የ20 አመት እስር ተፈርዶበታል።

ባለቤቱም የአምስት አመት እስር ተፈርዶባታል።

የቀድሞ የማዳጋስካር ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ራማሃትራ የአምስት አመት የእስር ቅጣት ተበይኖባቸዋል።

ማዳጋስካር ከቅኝ ገዥዋ ፈረንሳይ ነፃነቷን ከተጎናፀፈችበት ከአውሮፓውያኑ 1960 ጀምሮ በርካታ መፈንቅለ መንግሥቶችን አስተናግዳለች።