በአውስትራሊያ የወፎች ዝማሬ በሙዚቃ ደረጃ ዝርዝር ላይ ክብረ ወሰን ሰበረ

በሙዚቃ አልበሙ ከተካተቱት ሊጠፉ ከተቃረቡት አእዋፋት መካከል የምትገኘው ጋንግ-ጋንግ ኮካቱ የተባለችው ወፍ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በሙዚቃ አልበሙ ከተካተቱት ሊጠፉ ከተቃረቡት አእዋፋት መካከል የምትገኘው ጋንግ-ጋንግ ኮካቱ የተባለችው ወፍ
ታትሟል

በአውስራሊያ ለመጥፋት የተቃረቡ ወፎች የሚያዜሟቸው ዝማሬዎች ተቀርጸው እንደ ሙዚቃ ቀርበዋል።

የወፎቹ ዝማሬ እንደ ሙዚቃ መቅረቡ ሳይሆን ያነጋገረው ዝማሬያቸው በአውስትራሊያ የሙዚቃ ደረጃ ዝርዝር (ቻርት) ላይ ክብረ ወሰን መስበሩ ነው።

በአውስራሊያ የሙዚቃ ደረጃ (አሪያ ሙዚክ ቻርት) ከአምስቱ ከፍተኛ ተወዳጅ ሙዚቃዎች አንዱ የወፎቹ ዝማሬ ለመሆን በቅቷል።

የመጥፋት ዜማ ወይም 'ሶንግስ ኦፍ ዲሳፒራንስ' የሚል የአልበም ስም የተሰጠው ይህ ሙሉ በሙሉ የመጥፋት አደጋ ላይ ከሚገኙ ወፎች ዜማ የተቀናበረው ሥራ እጅግ ስመጥር ዘፋኞችን በልጦ በደረጃ ሰንጠረዡ ማማ ላይ ለመውጣት በቅቷል።

የወፎቹ ዝማሬ ከሙዚቃ ደረጃ ዝርዝሩ ውስጥ ከበለጣቸው ሥመ ጥር ዓለም አቀፍ አቀንቃኞች መካከል ትውልደ ኢትዮጵያዊው ካናዳዊ ዘ ዊክኢንድ (አቤል ተስፋዬ)፣ የስዊድኖቹ ዝነኛ የሙዚቃ ቡድን (አባ)፣ የገና በዓል (ክሪስማስ) ተወዳጅ ዘፋኞች ማይክል በብል እና ማሪያህ ኬሪ ይገኙበታል።

በአውስራሊያ በርድላይፍ ማኅበር የቀረበው ይህ የወፎች ዝማሬ አልበም 53 ዝርያቸው ሊጠፋ የተቃረቡ ወፎች ተሳትፈውበታል።

የአንዳንዶቹን ወፎች ዝማሬ ለመቅዳት ሰዓታትን ብቻ ሳይሆን ቀናትን መጠበቅ አስፈልጓል ተብሏል።

የዱር ወፎች ዝማሬ አቀናባሪ ዳቪድ ስቴዋርት እንደሚለው ይህን ቅንብር ለማሰናዳት 30 ዓመት አስፈልጓል።

የወፎቹ ዝማሬ አልበም ለሕዝብ የቀረበው ከሳምንት በፊት ነበር። በማኅበራዊ ሚዲያ አልበሙ ከተዋወቀ በኋላ ከፍተኛ ተቀባይነትን አግኝቷል።

ይህ የአእዋፋቱ ዝማሬ በአውስራሊያ ታሪክ ብቻም ሳይሆን በዓለም ታሪክ አዲስ የሙዚቃ ክብረ ወሰን ለመያዝ እንደቻለ ተነግሯል።

በአውስትራሊያ ከሚገኙ 6 ወፎች አንዱ የመጥፋት አደጋ ተጋርጦበታል። ዋናው ምክንያት ደግሞ የአየር ንብረት ለውጥ ነው። የወፎቹ አልበም የተቀናበረውም ይህን ግንዛቤ ለመፍጠር ነው።