በእንግሊዝ በኮቪድ ኦሚክሮን ዝርያ አማካኝነት የመጀመሪያው ሞት ተከሰተ

ታትሟል

የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር የኮቪድ19 አዲስ ዝርያ በሆነው ኦሚክሮን አማካኝነት ቢያንስ የአንድ ሰው ህይወት ማለፉን አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በአዲሱ ዝርያ ምክንያት ሆስፒታል የገቡ ሰዎች መኖራቸውን እና ይህንንም ለመቀነስ ዜጎቻቸው የመከላከል አቅምን የሚጨምር ክትባት እንዲወስዱ ጠይቀዋል።

የጤና ሚኒስትር የሆኑት ሳጂድ ጃቪድ በበኩላቸው ኦሚክሮን በአሁን ሰአት በእንግሊዝ ካሉ የኮቪድ 19 ታማሚዎች ውስጥ የ20 በመቶውን ድርሻ መያዙን ለፓርላማ አባላት ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ በቀጣይ ሁለት ሳምንታት ውስጥ በእንግሊዝ የሚኖሩ አዋቂ ሰዎች በሙሉ የመከላከል አቅምን የሚጨምር ክትባት ለማድረግ አቅደዋል።

ቦሪስ ዜጎቻቸው ኦሚክሮን የሚስፋፋበትን ከፍተኛ ፍጥነት ከግምት ውስጥ እንዲያስገቡ እና እምብዛም ህመም የማያስከትል ዝርያ ነው የሚለውን ሃሳብ ወደ ጎን እንዲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በትዊተር ገጸቸውም «የማይታመን ተግባር» ሲሉ በገለጹት ክስተት ግማሽ ሚሊዮን ዜጎች ሰኞ ቀን ብቻ የመከላከል አቅምን የሚጨምር ክትባት ለመውሰድ ወረፋ መያዛቸውን ተናግረዋል።

እስከ ትናንት ሰኞ ድረስ ባለው መረጃ በለንደን ካለው አጠቃላይ የኮቪድ ህሙማን ቁጥር ውስጥ 44 በመቶው የኦሚክሮን ዝርያ መሆኑ የተረጋገጠ ሲሆን በቀጣይ 48 ሰዓታት ውስጥም ኦሚክሮን ዋነኛው ዝርያ ሆኖ ይቀጥላል ተብሎ ይጠበቃል።

የአገሪቱ ፓርላማም መንግሥት ዝርያው እያስከተለ ያለውን ቀውስ መግታት እንዳለበት ድምጽ ለመስጠት ዛሬ ማክሰኞ ይሰበሰባል ተብሎ ይጠበቃል።

የወግ አጥባቂ ፓርቲ አባላት ያምጻሉ ተብሎ ቢጠበቅም የሌበር ፓርቲ መሪው የፓርቲያቸው ቀዳሚ ኃላፊነት የሚወሰዱ እርምጃዎችን መደገፍ እንደሆነ በመግለጽ የመከላከል አቅምን የሚጨምር ክትባት ዘመቻውን እንደሚደግፉ እና ዜጎችም እንዲከተቡ በቴሌቪዥን በተላላፈ ንግግራቸው ላይ ጥሪ አቅርበዋል።

የጤና ሚንስትሩ የመንግሥት ቀዳሚ ትኩረት አስቸኳይ የህክምና እና የክትባት ፍላጎቶች እንደሚሆኑ ጠቁመዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ እንደተናገሩት የጤና ሰራተኞች የምደባ ስራ ግን የካንሰር ህሙማንን እንደማይመለከት ተናግረዋል።

የጤና ሚኒስትሩ ጃቪድ የመከላከል አቅምን የሚጨምር ክትባት ከፍተኛ መጠን ያለውን የአገሪቱን የጤና ሰራተኞች ቁጥር እንደሚጠይቅ እና ይህም በመጪው ሁለት ሳምንታት ውስጥ ሁሉም ሰው ክትባቱን ያገኛል የሚል ማስተማመኛ ለመስጠትም የሚያስቸግር ያደርገዋል ብለዋል።

የአገሪቱ የጤና አገልግሎት ወደ ከፍተኛው የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት ዝግጁነት እንደሚመለስ እና ኦሚክሮንን ለመጋፈጥም አገራዊ የማስተባበር ስራ እንደሚሰራ ጃቪድ ተናግረዋል።