ናፍታሊ ቤኔት ለይፋዊ ጉብኝት ወደ ዩኤኢ በማቅናት የመጀመሪያው የእስራኤል መሪ ሆኑ

ታትሟል

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ናፍታሊ ቤኔት አገራቸው ከኢራን ጋር ያላት ግንኙነት ውጥረት ውስጥ ባለበት ጊዜ ወደ ዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ በማቅናት የመጀሪያው መሪ ሆኑ።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ዩኤኢ ከደረሱ በኋላ ከአቡ ዳቢ ልዑል አልጋ ወራሽ ሼክ ሞሐመድ ቢን ዛይድ ጋር ውይይት አድርገዋል።

እስራኤል እና ዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ ከአንድ ዓመት በፊት ግንኙነታቸውን ለማሻሻል ከስምምነት መድረሳቸው ይታወሳል።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ከአቡ ዳቢ ጋር ምጣኔ ሃብታዊ እና የንግድ ግንኙነትን ማሳደግ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ናፍታሊ ቤኔት አቡ ዳቢ የኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር ላይ ጠንካራ አቋም መያዝ አለባት ብለው ያሳስባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ የኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር ቢያሳስባትም ከቴህራን ጋር የተሻለ ወዳጅነትን የመመስረት ፍላጎት አላት።

ይሁን እንጂ እአአ 2018 ላይ የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ከኢራን ጋር ተደርሶ የነበረው የኒውክለር ስምምነት ጥሎ ሲወጣ፤ ዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ እና እስራኤል እርምጃውን ደግፈው ነበር።

ኢራን በኒውክሌር እንቅስቃሴዋ ላይ ገደብ ጥላ በምላሹ ተጥሎባት የሚገኙ ዓለም አቀፍ ማዕቀቦች እንዲነሱላት ከቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ሩሲያ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካ ጋር ውል ይዛ ነበር።

ይሁን እንጂ የትራምፕ አስተዳደር ይህን ስምምነት ጥሎ ከወጣ በኋላ ኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብሯን አስቀጥላለች።

ኢራን በተደጋጋሚ የኒውክሌር ኃይል የምታበለጽገው ለሰላማዊ ጉዳዮች ነው ትላለች።

የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር አሸማጋይነት ዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ እና እስራኤል ወዳጅነታቸውን ለማደስ ከስምምነት ደርሰው ነበር።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የቤኔትን ጉብኝት 'ታሪካዊ' ሲል ጠርቶታል።

ሼይክ ሞሐመድ በበኩላቸው የጠቅላይ ሚንስትሩ ጉብኝት የሁለቱ አገራት ሕዝብ ለማቀራረብ ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖራዋል ስለማለታቸው ተዘግቧል።