በሞሮኮ የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል ወሲብ የጠየቁ መምህራን ክስ ተመሰረተባቸው

ታትሟል

በሞሮኮ የተማሪዎችን ውጤት ለማስተካከል ወሲባዊ ግንኙነትን ጠይቀዋል የተባሉ አራት የዩኒቨርሲቲ መምህራን ፍርድ ቤት መቅረባቸው ተሰምቷል።

መምህራኑ ስነ-ምግባር በማጉደል፣ ጾታዊ አድልዎ ማድረግ እንዲሁም ሴቶች ላይ ጥቃት መፈጸም የሚሉ ክሶች ቀርበውባቸዋል።

በሞሮኮው አንጋፋ ዩኒቨርሲቲ መምህራን የሆኑት ግለሰቦች እስካሁን ድረስ የቀረበባቸውን ክስ አልስተባበሉም።

ሞሮኮ ውስጥ የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል ወሲብ መጠየቅ አዲስ የሚባል ነገር ባይሆንም መምህራን ግን ክስ ተመስርቶባቸው ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ግን እምብዛም የተለመደ አይደለም።

ክስ የቀረበባቸው መምህራን የሚያስተምሩበት ዩኒቨርሲቲ ከካዛብላንካ 80 ኪሎ ሜትር ርቀት በምትገኘው ሴታት ከተማ ውስጥ ይገኛል።

ክስ ከቀረባበቸው አራት መምህራን በተጨማሪ አምስተኛ መምህር ጥቃት በመፈጸምና ከባድ ወንጀል በመፈጸም ክስ ቀርቦበታል።

ይህ የመምህራን እና የአስተማሪዎች ግንኙነት ይፋ የሆነው ባሳለፍነው መስከረም ወር ላይ በማህበራዊ ሚዲያ በኩል አስተማሪዎቹ እና ተማሪዎቹ የተለዋወጡት መልዕክት ከተለቀቀ በኋላ ነው።

የቢቢሲ አረብኛ አርታኢ ሴኣስቺያን አሸር እንደሚለው ክስተቱ በሞሮኮ በርካቶችን አስቆጥቷል። ነገር ግን በቅርብ ዓመታት ተመሳሳይ ቅሬታዎች በተደጋጋሚ መቅረባቸውን ተከትሎ የሞሮኮ ዩኒቨርሲቲዎች ጥሩ ስም የላቸውም።

የአሁኑን ክስ ለየት የሚያደርገው ደግሞ ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት መምጣቱ ነው። እስከዛሬ የቀረቡ ቅሬታዎች ለህዝብም ይፋ ሳይሆኑ ፍርድ ቤትም ሳይቀርቡ ነበር የሚያልፉት።

የመብት ተሟጋች ቡድኖች እንደሚሉት የትምህርት ቤት ውጤትን ለማስተካከል ጾታዊ ትንኮሳን መጠቀም በጣም የተንሰራፋ ጉዳይ ሲሆን ሴቶቹ ደግሞ ያጋጠማቸውን ነገር በይፋ ለመናገር ድፍረቱ የላቸውም። ብዙውን ጊዜም ጾታዊ ትንኮሳ የደረሰባቸው ሴት ተማሪዎች ጉዳዩን በሚስጥር ነው የሚይዙት።

ይህ ደግሞ ከቤተሰብም ሆነ ከማህበረሰቡ ከሚደርስባቸው ጫና አንጻር እንደሆነ የመብት ተሟጋቾቹ ያስረዳሉ።