በቀጥታ ሥርጭት ላይ የጋዜጠኛዋን 'መቀመጫ' የመታው ጣሊያናዊ ደጋፊ ከስፖርታዊ ውድድሮች ታገደ

ታትሟል

ጣሊያናዊው የእግር ኳስ ደጋፊ በቀጥታ የቴሌቪዥን ሥርጭት ላይ የነበረች ጋዜጠኛን 'መቀመጫ' መምታቱን ተከትሎ ለሦስት ዓመታት በስፖርታዊ ዝግጅቶች ላይ እንዳይገኝ የጣሊያን ፖሊስ እገዳ ጥሎበታል።

በፍሎረንስ ከተካሄደው የሴሪ አ ጨዋታ በኋላ ግለሰቡ ፊቷን ወደ ካሜራ አዙራ ዘገባ ላይ የነበረችውን ጋዜጠኛ ግሬታ ቤካግሊያ ለመምታት እጁን ሲያንቀሳቅስ ታይቷል።

የቅዳሜው ክስተት ቁጣን ሲቀሰቅስ ብዙዎችም ከጋዜጠኛዋ ጎን ቆመዋል።

የቶስካና ቲቪ ባልደረባ የሆነችው ቤካግሊያ አቤቱታዋን ያቀረበች ሲሆን ፖሊስም ጉዳዩን በመመርመር ላይ ይገኛል።

ኢምፖሊ ፊዮረንቲናን 2 ለ 1 ካሸነፈበት ጨዋታ በኋላ ደጋፊዎቹ ስታዲየም ለቀው ሲወጡ ነው ግለሰቡ በጋዜጠኛዋ አካላዊ ትንኮሳ የፈፀመው።

"ይህን ማድረግ አትችልም። አዝኛለሁ።" ስትል ጋዜጠኛዋ በቪዲዮው ላይ ለሚታየው ግለሰብ ተናግራለች።

ከቆይታ በኋላ የቴሌቭዥኑ ዋና ዜና አንባቢ ጆርጂዮ ሚሼልቲ በሥርጭቱ ወቅት ወደተፈጠረው ክስተት እንዳትሻገር ለቤካግሊያ ነገሯታል። ሚሼልቲ በሰጠው በአስተያየት የተወቀሰ ሲሆን ቶስካና ቲቪም ከፕሮግራሙ "ሙያዊ እረፍት" ይወስዳል ብሏል።

ሚሼልቲ በበኩሉ ቤካግሊያን ለመከላከል እየሞከረ እንደሆነ ገልጾ "በቅዳሜው የቀጥታ ሥርጭቱ ወቅት ለተጠቀምኳቸው አሳዛኝ ቃላት" ይቅርታ እጠይቃለሁ ብሏል።

ቤካግሊያ በካሜራ ባይቀረጽም ሌላ ግለሰብም ተመሳሳይ ተግባር ሊፈጽምባት እንደሞከረ ቅሬታዋን አቅርባለች።

የቅዳሜው ክስተት ያጋጠመው የጣሊያን ከፍተኛ ሊግ እና ተጫዋቾች በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት በማውገዝ ዘመቻ ላይ በሚሳተፉበት ወቅት ነው። ሁሉም ተጫዋቾች ጾታን መሠረት ያደረገ ትንኮሳን የመከላከል አጋርነታቸውን ለማሳየት ፊታቸው ላይ ቀይ ቀለም ተቀብተው ታይተዋል።

ይህን ተግባር ፈጽሟል የተባለው ግለሰብ የፊዮረንቲና ደጋፊ የሆነው አንድሪያ ሴራኒ ተብሎ ተገልጿል።

የወንጀል ክስ ሊመሰረትበት የሚችል ሲሆን የፍሎረንስ ፖሊስ ኮሚሽነር የማግለያ ትዕዛዝ አውጥቷል። ዳስፖ በመባል የሚታወቀው ትዕዛዝ ለሦስት ዓመታት የስፖርት ዝግጅቶች ወደሚካሄዱባቸው ቦታዎች እንዳይገባ ይከለክላል።

በጣሊያን ቲቪ ላይ ቃለ ምልልስ ያደረገው ሴራኒ ስህተት እንደሰራ አምኖ ቤካግሊያን ይቅርታ ጠይቋል። ሆኖም ድርጊቱ የጾታዊ ጥቃትን የሚመለከት መሆኑን ውድቅ አድርጓል።

ድርጊቱን የፈጸመው ከቡድኑ ሽንፈት በኋላ በተፈጠረ ንዴት እንደነበር አስረድቷል።

ከኮሬር ዴላ ሴራ ጋዜጣ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረገችው ቤካግሊያ በበኩሏ ሴራኒ በሰጠው አስተያየት ዙሪያ መናገር እንዲያቅታት ማድረጉን ገልጻለች።

"በእርግጥ ምንም ስህተት ያልሠራህ ይመስልሃል?" ስትልም ጠይቃለች።

ቤካግሊያን ሕጋዊ እርምጃ ስትወስድ እንደሚደግፋት ቶስካና ቲቪ አስታውቋል።