ኮቪድ -19 ፡ የኮቪድ ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ ከሁለት ሴቶች አንዷ ጥቃት እንደደረሰባት ዩኤን ውመን አመለከተ

መስኮት አጠገብ የቆመች ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከጀመረ አንስቶ ከሁለት ሴቶች በአንዷ ላይ ጥቃት እንደተፈፀመባቸው አንድ ሪፖርት አመለከተ።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሴቶች ጉዳይ የሚከታተለው ዩኤን ውሜን የወጣው ይህ አዲስ ሪፖርት ወረርሽኙ በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን አባብሷል ብሏል።

ድርጅቱ ፆታን መሰረት ያደረገ ጥቃት በመቃወም በሚካሄደው የ16 ቀን ዘመቻ ማስጀመሪያ ዋዜማ ላይ ይፋ ባደረገው አዲስ ሪፖርት እንዳመለከተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከጀመረ አንስቶ ከሁለት ሴቶች በአንዷ ላይ ጥቃት ደርሶባታል፤ አሊያም ከሚያውቋቸው ሁለት ሴቶች አንዷ ጥቃት አጋጥሟታል።

ሪፖርቱ አክሎም በቤት ውስጥ በአዋቂዎች መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶች፣ ማስፈራሪያ እና አካላዊ ጥቃቶች በመጨመራቸው ሴቶች በቤት ውስጥ ብዙም ደኅንነት እንደማይሰማቸው ገልጸዋል ብሏል።

እንደ ሪፖርቱ ከሆነ ከአስር ሴቶች ሰባቱ ወረርሽኙ ከተከሰተ አንስቶ የቤት ውስጥ ጥቃት እንደጨመረም ያምናሉ።

ከአምስት ሴቶች ሦስቱ ደግሞ ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች የሚፈፀም ወሲባዊ ትንኮሳ ተባብሷል ብለው ያስባሉ። ይህም ወረርሽኙ ከጀመረ አንስቶ ሥራ እንዳይሰሩ፣ መሠረታዊ እና መዝናኛ አገልግሎቶች እንዳያገኙ ማድረጉን ሪፖርቱ ገልጿል።

ይሁን እንጂ በቤት ውስጥ ጥቃት ቢያጋጥማቸው የፖሊስ እርዳታን የሚፈልጉት ከአስር ሴቶች አንዷ ብቻ ናት። ሌሎቹ ሴቶች ከፖሊስ ይልቅ ከቤተሰባቸው እርዳታ መጠየቅን እንደሚመርጡ ተናግረዋል።

በሪፖርቱ ከአምስት ሴቶች ሁለቱ ደግሞ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ አጠቃላይ የአዕምሮ እና የስሜት ጤንነታቸውን እንዳወከው ገልጸዋል።

58 በመቶ የሚሆኑት ወረርሽኙ ከተከሰተ በኋላ ጥቃት የደረሰባቸው አሊያም ጥቃት የደረሰባትን ሴት የሚያውቁ ሴቶች የምግብ ዋስትና ችግር የመጋለጥ እድላቸውም ከፍተኛ እንደሆነም ሪፖርቱ አስረድቷል።

ወረርሽኙ ከተከሰተ አስንስቶ ከ13 አገራት በተሰበሰበ መረጃ ላይ ተመስርቶ የወጣው ይህ ሪፖርት ከወረርሽኙ በኋላ ጥቃት እንደደረሰባቸው የተናገሩ አሊያም የደረሰባቸው ሴቶች ዝቅተኛ እና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን አገራት ለይቷል።

በዚህም መሠረት ኬንያ 80 በመቶውን በመያዝ በግምባር ቀደምትነት ተቀምጣለች። ሞሮኮ 69 በመቶ ሁለተኛ፣ ናይጄሪያ በ48 በመቶ በአራተኛ ደረጃ፣ ካሜሩን 37 በመቶ በስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

ኮትዲቯር 29 በመቶ በአስረኛ ደረጃ ፣ ፓራጓይ ደግሞ 25 በመቶ ጥናቱ ከተካሄደባቸው አስራ ሦስት አገራት በመጨረሻ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃትን በመቃወም የሚካሄደው የ16 ቀናት ዘመቻ ሐሙስ ዕለት ተጀምሯል።

የዘንድሮው ዓመት መፈክርም "ዓለምን ብሩህ እናድረጋት፤ በሴቶች ላይ የሚደርስ ጾታዊ ጥቃት ይቁም" የሚል ነው።