ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሱዳን በወታደራዊው መንግሥት ላይ በተካሄደ ተቃውሞ 14 ሰዎች ተገደሉ
ሱዳን ውስጥ ከሳምንታት በፊት በተካሄደው መፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የተቆናጠጡትን ጄኔራል አብዱል ፋታህ አል ቡርሐንን ለመቃወም አደባባይ ከወጡ ሰልፈኞች መካከል 14ቱ ተገደሉ።
የአገሪቱ ሐኪሞች እንደገለጹት ሁሉም ሰልፈኞች የተገደሉት ጥይት ተተኩሶባቸው ነው።
በሱዳን የሲቪል አስተዳደር ገሸሽ ተደርጎ መፈንቅለ መንግሥት ከተደረገ በኋላ የማኅበረሰብ አንቂዎች ሕዝቡ አደባባይ ወጥቶ ተቃውሞውን እንዲገለጽ በጠየቁት መሠረት ነው ሰልፈኞች ወደ አደባባይ እየወጡ ያሉት።
ያለፈው ወር መፈንቅለ መንግሥትን የመሩት ጄኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሐን በጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ የሚመራውን ሲቪል አስተዳደር ካባረሩ በኋላ በርካታ ፖለቲከኞችን በማሰር ራሳቸውን ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት መሪ አድርገው ሾመዋል።
እርሳቸው የሥልጣኑን መንበር ከያዙ ወዲህ የፀጥታ ኃይሉ በተቃዋሚዎች ላይ በሚወስዳቸው እርምጃዎች እየጨከነ መጥቷል እየተባለ ነው።
በዋና ከተማዋ ካርቱም የሚገኙ ሐኪሞች ለዜና ወኪሎች እንደተናገሩት ፖሊስ የቆሰሉ ሰልፈኞች እንኳ ሕክምና እንዳያገኙ ሆስፒታል ግቢ ሳይቀር አስለቃሽ ጭስ ሲተኮስ ነበር።
መንግሥት የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ካቋረጠ በኋላ በከተማዋ አንዳንድ ሰፈሮች እየገባ በርካታ የጅምላ እስር እየፈጸመ እንደሆነም ተመላክቷል።
ጄነራል አልቡርሐን የአገሪቱን የመሪነት ሥልጣን በጉልበት በእጃቸው ካስገቡ ወዲህ የትኛውም አይነት የተቃውሞ እንቅስቃሴ ከፍ ወዳለ ደረጃ እንዳያድግ የሚቻላቸውን ሁሉ እያደረጉ ይገኛሉ።
የቀድሞው የሱዳን አምባገነን መሪ ኡመር አልበሽር ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ ሕጋዊ የሲቪል አስተዳደር ለማቆም የተደረጉ ጥረቶችን በሙሉ አልቡርሐን ወደ ኋላ እየመለሷቸው እንደሆነም ተዘግቧል።
ነገር ግን ከአልበሽር ውድቀት በኋላ በአገሪቱ የዴሞክራሲ ለውጥ እንዲካሄድ እና በነጻ ምርጫ አዲስ መንግሥት እንዲመሰረት ሲጥሩ የቆዩት ፖለቲከኞችና የማኅበረሰብ አንቂዎች አዲሱን ወታደራዊ መንግሥት እየተቃወሙ ነው።
የተቃውሞ ድምጾች በየዕለቱ በጄነራል አልቡርሐን ወታደራዊ አስተዳደር ላይ እየተሰማ ሲሆን በአገሪቱ ውስጥም አለመረጋጋት በርትቷል።
የቀድሞው ሲቪል አስተዳደር ባለሥልጣናት በወታደራዊው መንግሥት ቁጥጥር ስር ሲሆኑ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብደላ ሐምዶክ ደግሞ በቤታቸው ውስጥ በቁም አስር ላይ ይገኛሉ።