በአሜሪካ በአንድ ዓመት ብቻ መድኃኒትን ከመጠን በላይ በመውሰድ 100ሺህ ሰዎች ሞቱ

ታትሟል

ከ100ሺህ በላይ የሚሆኑ አሜሪካዊያን ካልተገባ የመድኃኒት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ በተለይም መድኃኒት ከመጠን በላይ በመውሰድ (overdose) መሞታቸው ይፋ ሆነ፡፡

ከመቶ ሺህ ዜጎች በላይ የሞቱት በተለይም በኮቪድ ወረርሽኝ እንቅስቃሴ ገደቦች በተጣሉባቸው ወራት ነው፡፡

በአሜሪካ ታሪክ ይህ አሐዝ ከፍተኛው ነው ብለዋል የመድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣናት፡፡ከመጠን ያለፈ መድኃኒት በመውሰድ የሞት አሐዝ በዚህ ዓመት በ28 እጅ ጨምሯል፡፡

ባለሙያዎች እንደሚሉት ከልክ ያለፈ መድኃኒት በመውሰድ የሞት መጠን ሊጨምር የቻለው በእንቅስቃሴ ገደቡ ወቅት በርካታ ዜጎች የሥነ ልቦና ምስቅልቅል ውስጥ በመግባታቸው ነው፡፡

በተለይም ድብታምና ሱሰኝነት የሞት አሐዙ እንዲመነደግ ምክንያት ሳይሆኑ አልቀረም፡፡

በነዚህ ከመጋቢት እስከ መጋቢት በነበሩ ወራት ውስጥ መድኃኒትን ከመጠን በላይ መውሰድ ያልጨመረው ከ50 የአሜሪካ ግዛቶች ውስጥ በአራቱ ብቻ ነው፡፡

የሞት ሰርተፍኬቶችን ዋቢ አድርጎ በወጣ አንድ ሰነድ እንደተመላከተው ከሚያዝያ 2020 እስከ ሚያዝያ 2021 ብቻ በአሜሪካ 100ሺህ 306 ሰዎች ያለ መጠን መድኃኒት ወስደው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡

በዚህ ዘመን በአሜሪካ ዋንኛ የሞት መንስኤ ከሆኑት የጦር መሣሪያ፣ የመኪና አደጋ እንዲሁም የጉንፋን በሽታም በላይ መድኃኒትን አብዝቶ መውሰድ (overdose) ዜጎችን እየጨረሰ ነው፡፡

መድኃኒትን ከመጠን በላይ መውሰድ አልፎ አልፎ በስህተት የሚከሰት ቢሆንም ብዙውን ጊዜ ሆን ተብሎ የሚደረግ ራሱን የቻለ የጤና ቀውስ ነው፡፡

በተለይም ህመምን የሚያስታግሱ ብዙዎቹ መድኃኒቶች አንድ ጊዜ መወሰድ ከጀመሩ ወዲህ ሱስ የሚያሲዙ በመሆናቸው ሰዎች ከቁጥጥር ውጭ በሆነ መንገድ ደጋግመው ይወስዷቸዋል፡፡

ሄሮይንና ኮኬይንን የመሰሉ አደገኛ እጽ ሱሰኞች በተለይ እነዚህ በሌሉ ጊዜ ሌሎች መድኃኒቶችን ደጋግመው በመውሰድ ሱሳቸውን ለማስታገስ ይሞክራሉ፡፡