በግብፅ ከአራት ሺህ ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረ ቤተ-መቅደስ ተገኘ

ታትሟል

ግብፅ ውስጥ 4,500 ዓመታትን ያሰቆጠረ ቤተ-መቅደስ በቁፋሮ ተገኘ።

ይህን ተከትሎ በግብፅ የሚገኙ አርኪዮሎጂስቶች በአስርት ዓመታት ውስጥ በጣም ወሳኝ ከተባሉት ግኝቶች መካከል አንዱን ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

ፈርዖኖች ወደ ህያው አማልክትነት እራሳቸውን ለመቀየር በመሞከር በህይወት እያሉ ከገነቧቸውና ከጠፉት አራቱን የፀሐይ ቤተ-መቅደሶች አንዱን አግኝተዋል።

ከ4 ሺህ 500 ዓመታት በፊት በግብፃውያን ፈርዖኖች የተገነቡ የፀሐይ ቤተ-መቅደሶች በቁጥር ስድስት ብቻ እንደሆኑ ይታመናል።

ከእነዚህ ውስጥ ሁለቱ ብቻ ነበሩ እስካሁን ድረስ የተገኙት። አርኪዮሎጂስቶች ሦስተኛውን ማግኘታቸው በ50 ዓመታት ውስት ትልቁ ግኝት እንደሆነ ይገልጻሉ።

ቤተ-መቅደሱ ከካይሮ በስተደቡብ በሚገኘው አቡ ጎራብ በተባለ ቦታ ላይ የተገኘ ሲሆን በውስጡም ረጅም ሐውልት ያለው ትልቅ ግቢ ነው።

ግዙፍ ፒራሚዶች የተነደፉት ከሞት በኋላ ባለው ህይወት ውስጥ የፈርዖኖችን አምላክነት ለማረጋገጥ በማለም ነው። የፀሐይ ቤተ-መቅደሶች ትናንሽ ሕንጻዎች ቢሆኑም እነሱን እንደ ህያው አማልክት ለማስቀመጥ የታሰቡ ናቸው።

በተለያዩ ጊዜያት በግብፅ ውስጥ በሚካሄዱ የአርኪዮሎጂ ፍለጋዎች ከመሬት በታች የተቀበሩና በሺህ የሚቆጠሩ ዓመታት ዕድሜ ያላቸውን የሥነ ሕንጻዎች በቁፋሮ ይገኛሉ።