ሰሜን ኮሪያ ከጃፓን በቅርብ ርቀት ወደሚገኝ የውሀ አካል ባሊስቲክ ሚሳኤል ተኮሰች

የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን

የፎቶው ባለመብት, KCNA

የምስሉ መግለጫ, የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን
ታትሟል

ሰሜን ኮሪያ ከጃፓን በቅርብ ርቀት ወደሚገኝ የውሀ አካል ቢያንስ አንድ ባሊስቲክ ሚሳኤል መተኮሷን የደቡብ ኮሪያ እና የጃፓን መከላከያዎች ገለጹ።

ይህ የሚሳኤል ሙከራ የተደረገው የደቡብ ኮሪያ፣ ጃፓን እና የአሜሪካ የደህንነት ኃላፊዎች በደቡብ ኮሪያ መዲና ስለ ሰሜን ኮሪያ ውይይት ካደረጉ በኋላ ነው።

በቅርብ ሳምንታት ፒዮንግያንግ እጅግ ፈጣን የሆኑ ሃይፐርሶኒክ እና ረጅም ርቀት ተጓዥ የሆኑ ናቸው የምትላቸውን ሚሳኤሎች እና ጸረ ከባድ መሳሪያዎችን መሞከርን ተያይዛለች።

አንዳንዶቹ ሙከራዎች በግልጽ ዓለም አቀፍ እገዳዎችን የጣሱ ናቸው።

ሰሜን ኮሪያ ምንም ዓይነት የባሊስቲክ ሚሳኤል እና የኒኩሌር መሳሪያዎችን እንዳትሞክር በተለይም በተባበሩት መንግስታት ማዕቀብ ተጥሎባታል።

ማክሰኞ ዕለት የደቡብ ኮሪያ ከፍተኛ ወታደራዊ ኃላፊዎች እንደገለጹት በምስራቃዊ ሰሜን ኮሪያ ከምትገኘው ሲንፖ ደሴት አቅራቢያ ሚሳኤል የተተኮሰ ሲሆን አካባቢውም ሰሜን ኮሪያ ሰርጓጅ መርከቦቿን በማዕከልነት የምትመራበት ቦታ ነው።

ሚሳኤሉም ኢስት ባህር ወይም የጃፓን ባህር ተብሎ በሚጠራው የውሃ አካል ላይ አርፏል።

ሁለት ባሊስቲክ ሚሳኤል መተኮሳቸውን የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚዮ ኪሺዳ የገለጸዑ ሲሆን ድርጊቱንም ''ከፍተኛ ቁጭት ውስጥ የሚያስገባ ነው'' ብለውታል።

ሰሜን ኮሪያ የሚሳኤል ሙከራዎቿን አጠናክራ የቀጠለች ሲሆን ደቡብ ኮሪያም ቢሆን የራሷን ረቂቅ መሳሪያዎች እያበለጸገች ነው። የአካባቢው ተንታኞችም ደቡብ እና ሰሜን ኮሪያ ወታደራዊ ፉክክር ውስጥ ስለመግባታቸው እየገለጹ ነው።

ሴዉል በቅርቡ ከሰርጓጅ መርከብ የሚተኮስ እጅግ ዘመናዊ ሚሳኤል ይፋ ያደረገች ሲሆን ይህም አገሪቱ ካደረገቻቸው ወታደራዊ ትዕይንቶች ትልቁ እንደሆነ ተገልጿል። በቅርቡም ደቡብ ኮሪያ የራሷን ሮኬት ወደ ህዋ ለማምጠቅ ደፋ ቀና እያለች ትገኛለች።

ሰሜን እና ደቡብ ኮሪያ በኮሪያ ጦርነት ምክንያት ከተለያዩ በኋላ ሁለቱ አገራት በጦርነት ጫፍ ላይ ሆነው ለበርካታ ዓመታት ቆይተዋል።

የሰሜን ከሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ባለፈው ሳምንት በኮሪያ ባህረሰጤ በድጋሚ ጦርነት እንዲቀሰቀስ እንደማይፈልጉ ገልጸው ነበር። ነገር ግን አገራቸው እራሷን አሜሪካን ከመሰሉ ጠላቶች ለመከላከል ስትል ከባድ መሳሪያዎችን እያበለጸገች እንደሆነ አስታውቀዋል።

ባለፉት 24 ሰአታት ደግሞ በሰሜን ኮሪያ የአሜሪካ ተወካዩ ሱንግ ኪም የጆ ባይደን አስተዳደር ከሰሜን ኮሪያ ጋር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለመነጋገር ዝግጅ ነው የሚለውን አቋም ገሸሽ አድርገውታል።

ከዚህ በፊት በነበሩ የአሜሪካ እና የሰሜን ኮሪያ ንግግሮች በዋነኛነት ሰሜን ኮሪያ የኒኩሌር መሳሪያዎች ማምረትና መሞከሯን ገታ እንድታደርገው ማስገደድ ላይ የተመሰረቱ ነበሩ።

አሜሪካ የተጣሉት ማዕቀቦች ከመነሳታቸው በፊት ሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር መሳሪያዎቿን ታስወግድ የምትል ሲሆን ሰሜን ኮሪያ ደግሞ በዚህ ሃሳብ በጭራሽ አልስማማም ብላ ቆይታለች።