አሜሪካ በአፍጋኒስታን በስህተት በድሮን ጥቃት ለተገደሉ ቤተሰቦች ካሳ ልትከፍል ነው

ታትሟል

ከጥቂት ወራት በፊት በአፍጋኒስታን መዲና ካቡል የአሜሪካ ጦር በድሮን ጥቃት በስህተት ለገደላቸው ለ10 ሰዎች ዘመዶች የገንዘብ ካሳ ሊሰጥ ነው።

ይህ የአሜሪካ ጦር ጥቃት የአገሪቱ ወታደሮች ከአፍጋኒስታን ከመውጣታቸው ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ የተፈጸመ ሲሆን አንድ የእርዳታ ሠራተኛና ሰባት ልጆቹን ጨምሮ ዘጠኝ የቤተሰቡን አባላት ለሞት የዳረገ ነበር።

ከገንዘብ ካሳው በተጨማሪ ከጥቃቱ የተረፉ ቤተሰቦችን ወደ አሜሪካ ለማዘዋወር እየሰራ እንደሆነ የአሜሪካው ጦር ዋና መሥሪያ ቤት ፔንታገን ገልጿል።

ከአይኤስ ታጣቂዎች ጋር ግንኙነት እንዳለው በማመን የሟቹን የእርዳታ ሠራተኛ መኪና የአሜሪካ የስለላ ድርጅት ለስምንት ሰዓታት ክትትል ሲያደርግበት ነበር።

በክትትሉም የሞቹ መኪና አይኤስ ጋር ይጠቀምበታል ተብሎ የሚታሰብ ግቢ ውስጥ እንደታየ እና በካቡል አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ከደረሰው ጋር ተያያዥነት ሊኖረው ይችላል በሚል መረጃ ነበር የጥቃት ኢላማ የሆነው።

የስለላው ድሮን የእርዳታ ሠራተኛው መኪናው ላይ ውሃ ሲጭን ያሳየ ቢሆንም ነገር ግን ክትትል የሚያደርጉት የስለላ ሠራተኞች ውሃው ፈንጂ ሊሆን ይችላል ብለው አምነው ነበር።

በወቅቲ የአሜሪካ ሠራዊት የማዕከላዊ ዕዝ አዛዥ ጄኔራል ማክኬንዚ ጥቃቱን "አሳዛኝ ስህተት" በማለት ገልጸውታል።

በድሮኑ ጥቃቱ ሲፈጸመው ከደረሰው ፍንዳታ በተጨማሪ ሁለተኛ ፍንዳታ የተሰማ ሲሆን የአሜሪካ ባለሥልጣናት ክስተቱ መኪናው በእርግጥ ፈንጂዎችን እንደያዘ ማረጋገጫ ነው ሲሉ ተደምጠው ነበር።

ሆኖም ከአደጋው በኋላ በተደረገ ምርመራ ሁለተኛው ፍንዳታ ምናልባት በመንገዱ ዳር ላይ በነበረ የነዳድ መያዣ ሳቢያ የተከሰተ ሳይከሰት እንዳልቀረ ተግምቷል።

በአሜሪካ የድሮን ጥቃት ከተገደሉት መካከል አንዱ ከአሜሪካ ወታደሮች ጋር በአስተርጓሚነት ይሰራ የነበረ ሲሆን ቀደም ሲል ለዓለም አቀፍ ድርጅቶች ይሰሩ የነበሩ አሜሪካ ለመግባት የሚያስችል ቪዛ የተሰጣቸው ሰዎችም በጥቃቱ ሞተዋል።

ለሞች ቤተሰቦች የቀረበው ካሳ የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር መስሪያ ቤትና በካቡል የሚንቀሳቀስ የእርዳታ ድርጅት ግንኙነት ከደረጉ በኋላ ነው ይፋ የተደረገው።

በምክክሩ የተሳተፉት የመከላከያ ሚኒስቴር የፖሊሲ ጉዳዮች ፀሐፊ ካህል በጥቃቱ የተገደሉት "ጥፋተኛ ያልሆኑ እና ከአይኤስ ጋር ግንኙነት የሌላቸው ወይም ለአሜሪካ ኃይሎች ስጋት ያልነበሩ ንፁሃን ናቸው" ሲሉ መነገራቸውን የመከላከያ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ ተናግረዋል።