ኢትዮጵያን ጨምሮ ከተለያዩ አገራት ገበያ እንዲወጣ የተባለው የአፕል ጭማቂ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በደቡብ አፍሪካ የሚመረተው ሲረስ የተባለው ታሸገ ጭማቂ ከፍተኛ መጠን ያለው ለጤና ጎጂ የሆነ ንጥረ ነገር በውስጡ በመገኘቱ ከሰባት የአፍሪካ አገራት ገበያ እንዲሰበሰብ መደረጉ ተዘግቧል።
የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን በበኩሉ ሲረስ አፕል ጁስ የተሰኘው ጭማቂ "በውስጡ ጎጂ የሆነ ከሻጋታ የመነጨ መርዛማ ኬሚካል ስለተገኘበት" ኅብረተሰቡ እንዳይጠቀም ማሳሰቢያ አውጥቷል።
ባለስልጣኑ ስለተገኘው መርዛማ ንጥረ ነገር በአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በኩል በሰጠው ማብራሪያ በፍራፍሬዎች ላይ የሚከሰት ማይኮቶክሲን ከሚባል ከሻጋታ የሚመነጭ መሆኑን አመልክቶ ኅብተሰቡ የተጠቀሰውን ምርት እንዳይጠቀም መክሯል።
በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ተመርቶ ወደ ተለያዩ የአፍሪካ አገራት የሚሰራጨው ሲረስ የአፕል ጭማቂ በመበስበስና በመሻገት የሚከሰተው ፓቱሊን የተባለው ጎጂ ንጥረ ነገር ስለተገኘበት ከገበያ እንዲወጣ እየተደረገ ነው።
በጭማቂው ላይ በተደረገ ቤተ ሙከራ ፍተሻ እንደተረጋገጠው ሲረስ በተባለው የአፕል ምርት ላይ በአንድ ሊትር ውስጥ እንዲኖረው ከተፈቀደው 50 ማይክሮ ግራም ከፍ ያለ መጠን መገኘቱ ተገልጿል።
ይህ የማይኮቶክሲን ውጤት የሆነው ፓቱሊን የተባለው ጎጂ ንጥረ ነገር በአፕል እና በአፕል ምርቶች ውስጥ በሚከሰቱ በተለያዩ ሻጋታዎች አማካይነት የሚፈጠረው።
በጭማቂው ውስጥ የተገኘው ንጥረ ነገር ፓቱሊን በተጠቃሚዎች ላይ ማቅለሽለሽና ማስታወክን በማስከተል ጤናን ሊያውክ ይችላል ተብሏል።
ይህ ሲረስ የተባለው የአፕል ጭማቂ በኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን አመልክቶ ኅብረተሰቡ እንዳይ ጠቀመውና በገበያ ላይ ከተገኘም ጥቆማ እንዲሰጠው ጥሪ አቅርቧል።
ምርቱ በተጨማሪም በኬንያ፣ በዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ በዛምቢያ፣ ዚምብብዌ፣ ኡጋንዳ፣ ሲሸልስ እና ሞሪሺየስ ገበያዎች ውስጥ ተሰራጭቶ እንደሚገን ተነግሯል።
የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ የንግድ ቀጠና (ኮሜሳ) የንግድ ውድድር ኮሚሽን በአገራቱ ውስጥ ያሉ የምርቱ ተጠቃሚዎች ባለፈው ሰኔ ወር ተመርተው የተሰራጩ የሲረስአፕል ጭማቂ ምርቶችን ከገበያ አስወጥተው ለአምራቹ እንዲመልሱ ጥሪ አቅርቧል።












