በኖርዌይ በቀስት በተፈጸመ ጥቃት አምስት ሰዎች ተገደሉ

ታትሟል

በኖርዌይ አንድ ሰው ቀስት ተጠቅሞ ባደረሰው ጥቃት አምስት ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ሁለት ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል።

ከሀገሪቱ ዋና ከተማ ኦስሎ በስተደቡብ ምዕራብ በሚገኝ አከባቢ ኮንግስበርግ በተባለ አከባቢ የደረሰውን ይህንን ጥቃት የ 37 ዓመቱ ዴንማርካዊ እንደፈጸመው በመጠርጠሩ በቁጥጥር ስር ውሏል።

ፖሊስ ድርጊቱን ብቻውን ያቀነባበረው እንደሆነ ግምቱን ያሰቀመጠ ሲሆን ጥቃቱን የሽብር ተግባር መሆኑን አለመሆኑን እየመረመረ ይገኛል።

የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ኤርና ሶልበርግ ድርጊቱ በተመለከተ የወጡ ሪፓርቶች "እጅግ አሰቃቂ ነበሩ" ብለዋል።

"ብዙ ሰዎች እንደሚፈሩ ተረድቻለሁ ፣ ግን ፖሊስ አሁን [ነገሮችን] በቁጥጥር ስር መዋሉን አጽንኦት መስጠት አስፈላጊ ነው" ብለዋል።

አጥቂው ጥቃቱን መሰንዘር የጀመረው በኮንግስበርግ ምዕራዊ ክፍል በኩል በአንድ ሱፐርማርኬት ውስጥ ነው ሲሆን ጉዳት ከደረሰባቸው ሰዎች አንዱ በወቅቱ መገበያያ ውስጥ የነበረና ከስራ ውጪ የሆነ የፖሊስ አባል ይገኝበታል።

የመገበያያው ቃል አቀባይ በስፍራው "ከባድ ክስተት" ተፈጥሮ እንደነበር አረጋግጠው አንድም ሠራተኛ ላይ የአካል ጉዳት አልደረሰም ብለዋል።

በፖሊስና በአጥቂው መካከል ግብግብ ከተፈጠረ በኋላ ተጠርጣሪው በቁጥጥር ስር ውሏል።

አንድ የዓይን እማኝ ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን አስተያየት ስትሰጥ ሁከት እንደሰማች እና አንዲት ሴት ራሷን ስትሸፍን መመልከቷንና "የሆነ ሰው ጥግ ላይ ቆሞ በትከሻ ላይ መስወንጨፊያ እና በእጁ ላይ ደግሞ ቀስት" ይዛ እንዳየች ተናግራለች።

"ሰዎች ሕይወታቸውን ለማዳን ሲሯሯጡ አይቻለሁ። ከሚሯሯጡት መካከል አንዷ ሕፃን የያዘች ሴት ናት" ስትል አክላለች።

ፓሊስ ጥቃት አድራሹ ሌላ መሳሪያ ስለመጠቀሙ ምርመራ እያደረገ ነው።