ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
"በርካታ ሕፃናትን ገድያለሁ" ያለው ኬንያዊ ከፖሊስ ጣቢያ አመለጠ
ከ10 በላይ ሕፃናትን መግደሉን ያመነው ኬንያዊው በመዲና ናይሮቢ ከሚገኝ አንድ ፖሊስ ጣቢያ ማምለጡ ተሰምቷል።
ማስተን ዋንጃላ ረቡዕ ዕለት በ14 ሕፃናት ግድያ መዝገብ ፍርድ ቤት መቅረብ ይጠበቅበት ነበር።
ግለሰቡ በዋና ከተማዋ ናይሮቢ እንዲሁም በምስራቅና ምዕራብ ኬንያ በሚገኙ ከተሞች ነው ሕፃናትን መግደሉን ያመነው።
ፖሊስ ግለሰቡ ማምለጡን ያወቀው ጥዋት በነበረው የታራሚዎች ቆጠራ ወቅት መሆኑን አስታውቋል።
ሰውዬው ፖሊስ ጣቢያ እንዲቆይ የተደረገው ፖሊስ የ14 ሕፃናትን ግድያ ወንጀል እየመረመረ ስለሆነ ነው ተብሏል።
ግለሰቡ ከጥቂት ወራት በፊት በቁጥጥር ሥር ውሎ በርካታ ሕፃናትን ገድሎ መጣሉን ያመነበት ዜና ብዙዎችን ያስደነገጠ ነበር።
ጆጎ ሮድ ከተሰኘው ፖሊስ ጣቢያ ግለሰቡ ባመለጠበት ወቅት ተረኛ የነረቡ የፖሊስ መኮንኖች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሶስቱ የፖሊስ አባላት ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበው እስረኛ እንዲያመልጥ በመርዳት ክስ እንደሚከፍትባቸው ተሰምቷል።
ፖሊስ በጣም አደገኛ ሰው ነው ብለው የፈረጀውን ግለሰብ አድኖ ለመያዝ ፍለጋውን መጀመሩን ይፋ አድርጓል።
ማስተን ዋንጃላ ባለፈው ሐምሌ ነበር ወንድ ሕፃናትን መርዝ በመግደል ወንጀል በቁጥጥር ሥር የዋለው። ሰውዬው የአንዳንዶቹን ደም ጠጥቻለሁ ሲልም ተናዟል።