ሰሜን ኮሪያ አዲስ ፈጣን 'ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል' አስወነጨፍኩ አለች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሰሜን ኮሪያ ማክሰኞ ዕለት ህዋሶንግ-8 የተባለ አዲስ ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል በተሳካ ሁኔታ መሞከሯን አስታወቀች።
የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን እንዳሉት አዲሱ ሚሳኤል በአምስት ዓመቱ የወታደራዊ ልማት ዕቅድ ከተዘረዘሩት "አምስት በጣም አስፈላጊ" መሣሪያዎች አንዱ ነው።
አዲሱን ሚሳይል 'ስትራቴጂካዊ መሣሪያ' ብለውታል። ይህም የኒውክሌር አቅም አለው ለማለት ነው።
የማክሰኞው ሙከራ በጠንካራ ማዕቀቦች ሥር የምትገኘው ፒዮንግያንግ የጦር መሣሪያ ቴክኖሎጂዋ እያደገ ስለመምጣቱ ምልክት ነው።
የሰሜን ኮሪያ የዜና ማሰራጫ ኬሲኤንኤ "የዚህ የጦር መሣሪያ መሠራት ... ሃገሪቱን በሁሉም ረገድ እራሷን የመከላከል አቅም ጨምሯል" ብሏል።
የአሁኑ ሙከራ በዚህ ወር ብቻ ሃገሪቱ ያደረገችው ሦስተኛው የሚሳኤል ሙከራ ነው። ቀደም ሲል አዲስ ክሩዝ ሚሳኤል እና ከባቡር ላይ የሚወነጨፍ አዲስ የባለስቲክ ሚሳኤል ስርዓት ይፋ አድርጋለች።
ስለአዲሱ ሚሳኤል ምን እናውቃለን?
ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሎች ከተለመዱት በጣም ፈጣን እና ቀልጣፋ ሲሆኑ በሚሳኤል የመከላከያ ሥርዓቶች ለመክሸፍም በጣም ከባድ ያደርጋቸዋል ሲል ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ዘግቧል።
የካርኔጂ ኢንዶውመንት ፎር ኢንተርናሽናል ፒስ ባልደረባ የሆኑት አንኪት ፓንዳ በዚህ ወቅት የሚሳኤሉን "ትክክለኛ አቅም" መገምገም ከባድ ነው ብለዋል። ሆኖም "ለባህላዊው ባለስቲክ ሚሳኤል መከላከያ ፈታኝ ሊሆን ይችላል" ሲሉ ገልጸዋል።
ስለ ሰሜን ኮሪያ የጦር መሣሪያ መርሃ ግብር ምን ይታወቃል?
የሰሜን ኮሪያ የቅርብ ጊዜ ሙከራዎች ሃገሪቱ የጦር መሣሪያ መርሃ ግብሯን ከፍ እያደረገች መሆኑን ያመለክታሉ።
ከትናንቱ ሙከራ በኋላ የሰሜን ኮሪያ መልዕክተኛ ኪም ሶንግ የሃገሪቱን የጦር መሣሪያ የማምረት መብት ደግፈው ተሟግተዋል።
በዓመታዊው የኒው ዮርክ የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ባደረጉት ንግግር ሃገሪቱ "ራሷን ለመከላከል እና የሃገሪቱን ደህንነት እና ሠላም በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ" ብሔራዊ መከላከያ እየገነባች ነው ብለዋል።
ሰሜን ኮሪያ በወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ዙሪያ ደቡብ ኮሪያን የተለያየ ገጽታ እያሳየች ነው በማለት ደጋግማ ትከሳለች።
ደቡብ ኮሪያ በቅርቡ ሰሜን ኮሪያን "ትንኮሳ" ለመከላከል አስፈላጊ ያለችውን የመጀመሪያውን የባሕር ሰርጓጅ መርከብ የባለስቲክ ሚሳኤል ሞክራለች።
አሜሪካ በበኩሏ ሰሜን ኮሪያ ኒውክሌር ማምረት እንድታቆም የጠየቀች ሲሆን ፒዮንግያንግ ከፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ጋር ያላት ግንኙነት በውጥረት የተሞላ ነው።
በጃፓን እና ሰሜን ኮሪያ መካከልም ውጥረት አለ።
ባለፈው ወር የተባበሩት መንግሥታት የአቶሚክ ኤጀንሲ እንዳስታወቀው ሰሜን ኮሪያ "በጣም አሳሳቢ" ያለውና ለኑክሌር መሣሪያዎች ፕሉቶኒየም ማምረት የሚያስችላትን ማብላያ እንደገና አስጀምራለች።












