ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ግብፅ ከዩቲዩብ ገቢ የሚያገኙ ዜጎቿ ግብር እንዲከፍሉ ልታደርግ ነው
ግብፅ በአገሯ የሚገኙ የተለያዩ ይዘቶች ያላቸውን ቪዲዮዎች በማኅበራዊ ሚዲያው መድረክ ዩቲዩብ ላይ በማጋራት ገቢ ያሚያገኙ ግለሰቦችን ግብር ልታስከፍል ነው።
በርካታ ተጠቃሚዎችን እየሳበ ያለውና በርካታ ተከታይና ተመልካች ላላቸው የቪዲዮ ማጋሪያ ገጾች ክፍያ የሚፈጽመው የማኅበራዊ ትስስር መድረክ ዩቲዩብ የከፍተኛ ገቢ ምንጭ እየሆነ ባለበት ጊዜ ነው ግብፅ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው።
ግብፅ የዩቲዩብ ገንዘብ ተጠቃሚዎች እንደማንኛውም ዜጋ ከሚያገኙት ገቢ ላይ ግብር እንዲከፍሉ እንደሚደረግ አሳውቋል።
የግብፅ መንግሥት እንዳለው ይህ ግብር ትኩረቱን የሚያደርገው በዓመት ከ500 ሺህ የግብፅ ፓወንድ ወይንም 32 ሺህ ዶላር በላይ ገቢ ከዩቲዩብ የሚያገኙት ላይ ነው።
ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ የአገሪቱ የግብር ባለሥልጣን የዩቲዩብ ይዘት አቅራቢዎችናና ብሎገሮችን እንዲመዘገቡና በዓመት የሚያገኙትን ገቢ እንዲያሳውቁ ጥሪ አቅርቧል።
ነገር ግን ይህ ግብር ዩቲዩብ ላይ የተለያዩ የቪዲዮ ይዘቶችን በማቅረብ ገቢ በሚያገኙት ግብፃውያን ዘንድ ተመሳሳይ ምላሽን አላገኘም።
የፈረንሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ እንደዘገበው የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ የሆኑ አንዳንድ ሰዎች የመንግሥትን እርምጃ ደግፈዋል።
ለዚህም ምክንያታቸውን ሲያስቀምጡ "ደሃ የአትክልት ቸርቻሪዎች ግብር እንዲከፍሉ እየተደረገ፤ ከፍተኛ ገቢ የሚያገኙ ሀብታሞችን ግብር እንዲከፍሉ ማድረግ ተገቢ ነው" በማለት ትዊተር ላይ ጽፈዋል።
ሌሎች ግን በአገሪቱ ያለውን የኢንተርኔት አቅርቦት ዋጋ ውድነትን በመጥቀስ የመንግሥትን ውሳኔ ተቃውመው ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሃሳባቸውን ገልጸዋል። ።
"መንግሥት የዩቲዩብ ተጠቃሚዎች ግብር እንዲከፍሉ የሚፈልግ ከሆነ ቢያንስ የተሻላ የኢንትርኔት አግልግሎት ማቅረብና የአገልግሎት ውስንነቶችን ማስወገድ አለበት" ሲሉ ይከራከራሉ።
በግብፅ የግብር ባለሥልጣን ውስጥ ከፍተኛ ኃላፊ የሆኑት ሚሐመድ አል-ጋያር እንዳሉት "በአገሪቱ ውስጥ በማንኛውም መስክል ላይ ተሰማርቶ ገቢ የሚያገኝ በተገቢው ሁኔታ ግብር ሊከፍል ይገባል" ሲሉ የመንግሥታቸውን ውሳኔ ግልጽ አድረገዋል።