ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሠሜን ኮሪያ 'የኑክሌር ጦር መሳሪያ እሽቅድድም' ሊቀሰቀስ ይችላል ስትል አስጠነቀቀች
ሠሜን ኮሪያ በአሜሪካ፣ በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) እና በአውስትራሊያ መካከል የተደረሰውን አዲስ የደኅንነት ስምምነት "የኑክሌር ጦር መሳሪያ እሽቅድድምን" ሊቀሰቅስ ይችላል በሚል ተቃወመች።
የሠሜን ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አንድ ባለሥልጣን እንዳሉት በሦስቱ አገራት መካከል የተደረሰው ስምምነት "በእስያ ፓሲፊክ አካባቢ ያለውን ስልታዊ ሚዛን ያናጋዋል" ብለዋል።
በዚህ ስምምነት አሜሪካና ዩናይትድ ኪንግደም ለአውስትራሊያ በኑክሌር ኃይል የሚንቀሳቀስ ሰርጓጅ መርከብ ለመገንባት የሚያስችል ቴክኖሎጂ እንድታገኝ የሚያስችል ነው።
ይህ ስምምነት በደቡብ ቻይና ባሕር አካባቢ ያለውን የቻይናን ተጽእኖ ለመቋቋም የታለመ ጥረት እንደሆነ በስፋት ይነገራል።
ባለፈው ሳምንት ይፋ የሆነው ይህ የሦስቱ አገራት ስምምነት የክሩዝ ሚሳኤል፣ የአውሮፕን ደኅንነት እና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን የሚያካትት ነው።
"ይህ ሁኔታ በእስያ ፓሲፊክ አካባቢ ያለውን ስልታዊ ሚዛን በማዛባት አላስፈላጊና አደገኛ ተከታታይ የኑክሌር ጦር መሳሪያ እሽቅድድምን ሊቀሰቅስ ይችላል" ሲሉ አንድ የሠሜን ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለሥልጣን የደኅንነት ስምምነቱን ተችተዋል።
ባለፈው ሳምንት ሠሜን ኮሪያ ሁለት ዋነኛ የረጅም ርቀት እና የባለስቲክ ሚሳኤል ጦር መሳሪያዎች ሙከራ አድርጋለች።
ቻይናም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ ቃል አቀባይ በኩል ስምምነቱ "የአካባቢውን ሰላም ክፉኛ የሚጎዳና. . . የጦር መሳሪያ እሽቅድድምን የሚያባብስ ነው" ስትል ተችታዋለች።
ሠሜን ኮሪያ "ቻይናን የመሰሉ አገራት እንዲህ አይነቱን የአካባቢውን ሰለምና መረጋጋት የሚያናጋ ኃላፊነት የጎደለውን ድርጊት ማውገዛቸው የሚጠበቅ ነው" ብላለች።
በስምምነቱ እንደተጠቀሰው አሜሪካ የሰርጓጅ መርከብ ቴክኖሎጂን ቀደም ሲል ለዩናይትድ ኪንግደም ብቻ ካጋራች ከ60 ዓመታት በኋላ ለአውስትራሊያ ለመስጠት ተስማምታለች።
በዚህም አውስትራሊያ ከመደበኛዎቹ ሰርጓጅ መርከቦች ፈጣን እና ለመለየት ከባድ የሆኑትን በኑክሌር ኃይል የሚንቀሳቀሱ ዘመናዊ ሰርጓጅ መርከቦችን ለመገንባት ያስችላታል።
መርከቦቹ በባሕር ውስጥ ለወራት መቆየት የሚችሉና ረጅም ርቀት የሚወነጨፉ ሚሳኤሎችን የሚሸከሙ ናቸው። አውስትራሊያ ግን መርከቦቹን የኑክሌር ጦር መሳሪያ እንዲታጠቁ የማድረግ ፍላጎት እንደሌላት ገልጻለች።
ሦስቱ አገራት የደረሱት የደኅንነት ስምምነት ይፋ በተደረገበት ጊዜ የቻይና ስም በቀጥታ ባይጠቀስም፤ የአገራቱ መሪዎች በተደጋጋሚ በአካባቢው ያለው የደኅንነት ስጋት "በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ" መምጣቱን ጠቅሰዋል።
ሠሜን ኮሪያ ቀደም ሲል ፈረንሳይ ስምምነቱን በተመለከተ "ከጀርባ መውጋት" ነው በሚል ያወጣችውን መግለጫ በመጥቀስ ስምምነቱ በአጋሮች መካከል ሳይቀር "ከባድ ቀውስን" አስከትሏል ብላለች።
ፈረንሳይ ከአራት ዓመት በፊት 12 መደበኛ ሰርጓጅ መርከቦችን ለመገንባት ከአውስትራሊያ ጋር በ37 ሚሊዮን ዶላር የደረሰችውን ስምምነት የሚያሰናክል በመሆኑ አጥብቃ ተቃውማዋለች።
ፈረንሳይ እንዳለችው ከሆነ በሦስቱ አገራት መካከል የተደረሰውን ስምምነት በተመለከተ የተነገራት ለሕዝብ ይፋ ከመደረጉ ከሰዓታት በፊት መሆኑን በመጥቀስ ቁጣዋን ገልጻለች።