ኢትዮጵያውያን አምስት ሚሊዮን ደብዳቤዎችን ለጆ ባይደን ሊልኩ ነው

ታትሟል

በትግራይ ጦርነት ላይ የአሜሪካን አስተዳደር ፖሊሲ ለማስቀየር በተያዘ ዘመቻ አምስት ሚሊዮን ደብዳቤዎችን ለፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ለመላክ እንቅስቃሴ መጀመሩ ተገለጸ።

"የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ መንግሥት" በሚል መሪ ቃል የተጀመረው አገር አቀፍ ዘመቻ እስከ መስከረም 15/ 2014 ዓ.ም እንደሚቀጥል አዘጋጁ የኢትዮጵያ ዩዝ ኢምፓወርመንት ማኅበርና አገር አቀፍ የወጣቶች ንቅናቄ ኃላፊ አለማየሁ ሰይፉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የድርጅቱ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ለቢቢሲ እንደገለጹት በጥቅምት መጨረሻ በተከሰው የትግራይ ጦርነት ከተጎዱ አካባቢዎች የመጡ የዓይን እማኞች "ከህወሓት ጋር ግንኙነት ባላቸው ታጣቂዎች የደረሰባቸውን ግፍ ይመሰክራሉ" ብለዋል።

አክለውም "የአሜሪካ መንግሥት በአገራችን የውስጥ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ መግባቱን ማቆም አለበት። ከአፍጋኒስታን፣ ከፓኪስታን እና ከሊቢያ መማር አለባቸው" ብለዋል አቶ አለማየሁ።

ፕሬዝዳንት ባይደን እና ሌሎች የምዕራባውያን መሪዎች ወደ ጎረቤት አማራ እና አፋር ክልሎች የተዛመተው የትግራይ ጦርነት እንዲያቆም ለኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጥሪ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።

ኢትዮጵያና አሜሪካ በትግራይ ቀውስ ውስጥ እየተደረጉ ስላሉ እርምጃዎች ተመሳሳይ አረዳድ የላቸውም።

በቀጣናው ከአልሻባብ መግነን ጋር ተያይዞ ሸብርተኝነትን ለመዋጋት በሚል የአሜሪካ ቀኝ እጅ የነበረችው ኢትዮጵያና አሜሪካ በትግራይ ባለው ቀውስ ምክንያት ግንኙነታቸው ጥያቄ ውስጥ ገብቷል።

አሜሪካ በኢትዮጵያና በኤርትራ የቀድሞ እና የአሁን ባለስልጣናት፣ ወታደራዊ እና ደኅንነት ኃላፊዎች እንዲሁም የአማራ ክልል መደበኛና ኢ-መደበኛ የጸጥታ አባላትና ግለሰቦች፣ ሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትን ባደናቀፉ የህወሓት አባላት ላይ የቪዛ እቀባ መጣሏ የሚታወስ ነው።

ከጉዞ እቀባው በተጨማሪ አሜሪካ የምታደርገውን የምጣኔ ሀብትና የደኅንነት እገዛ እንዲቋረጡና ግጭቱ ካልቆመና መሻሻሎች ካልታዩ፤ ተጨማሪ እርምጃዎችን እንደምትወስድም አስጠንቅቃለች።

ኢትዮጵያ በበኩሏ አሜሪካ ያሳለፈቻቸው እርምጃዎች የሁለቱንም አገራት የዘመናት ግንኙነት የሚጎዳ ነው ትላለች። ኢትዮጵያ የአሜሪካንን እርምጃዎች ያየችው በውስጥ ጉዳዮች ጣልቃ ገብነት ነው።

በዚህ ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተፈናቅለዋል እንዲሁም የምግብ እርዳታ በመታገዱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ በረሃብ አፋፍ ላይ ናቸው።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር ከህወሓት መሪዎች ጋር ለመደራደር የሚደረገውን ግፊት በተከታታይ ሲቃወመው ይሰማሉ።

የፌዴራል መንግሥት ወታደሮች ሆነ የአማፂያኑ ተዋጊዎች በተፈጸሙ በበርካታ ግፎች የሚከሰሱ ቢሆንም ሁለቱም ወገኖች ይህንን ያስተባብላሉ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ፓርቲ የደብዳቤ ዘመቻ የአሜሪካ እና የምዕራባውያን መንግሥታት የሚደረገው የቅርብ ጊዜ የሕዝብ ውግዘት ነው።