ፊፋ በእንግሊዝ ተጫዋቾች ላይ የተሰነዘረውን ጥቃት መመርመር ጀመረ

እንግሊዝ ሃንጋሪን 4 ለ 0 ባሸነፈችበት ጨዋታ ላይ በተጫዋቾች ላይ የተሰነዘረውን የዘረኝነት ጥቃት ለመመርመር ፊፋ ሥራ መጀመሩ ተነገረ።
ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ በሃንጋሪ ዋና ከተማ ቡዳፔስት ውስጥ በተካሄደው የእግር ኳስ ግጥሚያ ላይ የእንግሊዝ ተጫዋቾቹ ራሂም ስተርሊንግ እና ጁድ ቤሊንግሃም የዘረኝነት ጥቃት ኢላማ ሆነው ነበር።
ቡዳፔስት ውስጥ በሚገኘው ፑስካስ አሬና ስታዲየም በተደረገውና እንግሊዝ በሰፊ የግብ ልዩነት ባሸነፈችበት ጨዋታ ወቅት ተጨዋቾቹ ላይ የተለያዩ ነገሮች ከተመልካቾቹ ተወርውሮባቸዋል። ይህም የተከሰተው በጨዋታው ሁለተኛ አጋማሽ ላይ ነበር።
ከክስተቱ በኋላ ተጫዋቾቿ ላይ ጥቃት የተሰነዘረባት እንግሊዝ ድርጊቱን "ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው" ስትል አውግዛዋለች።
ለጀርመኑ ቡድን ቦሪሲያ ዶርትሙንድ የመሃል መስመር ተጫዋች የሆነው የ18 ዓመቱ ቤሊንግሃም ከጥቃቱ በኋላ የዘረኝነት ጥቃቱን በተመለከተ ትዊተር ላይ እንዳሰፈረው "የሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ተገቢውን የቅጣት እርምጃ ካልወሰዱ ድርጊቱ የጨዋታው አካል ሆኖ ይቀጥላል። ጥላቻ እንዲሰፍን ማድረግ የለብንም።" ብሏል።
የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰንም "እንዲህ አይነቱ አሳፋሪ ድርጊት እስከ መጨረሻው ከእግር ኳስ ሜዳዎች እንዲወገዱ በአጥፊዎች ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ መወሰድ አለበት" ሲሉ የዓለም እግር ኳስ የበላይ አካል የሆነውን ፊፋን ጠይቀዋል።
አርብ ከሰዓት በኋላ ፊፋ እንዳስታወቀው በእግሊዝና በሃንጋሪ ግጥሚያ ወቅት የነበረውን የጨዋታውን ሪፖርት ከመረመረ በኋላ በድርጊቱ ላይ የሥነ ሥርዓት እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ሂደት መጀመሩን አስታውቋል።
ጨምሮም ፊፋ የትኛውንም አይነት ዘረኝነት፣ መድልዎና ጥቃትን አጥብቆ የሚቃወምበት አቋሙ አሁንም ጽኑ እንደሆነ ገልጿል።
"በእግር ኳስ ውስጥ የሚከሰቱ እንዲህ አይነት ተቀባይነት የሌላቸው ተግባራትን ፈጽሞ አይታገስም" ሲል አቋሙን አሳውቋል።
የአውሮፓ የእግር ኳስ ማኅበር (ዩኤፋ) የሃንጋሪ ደጋፊዎች ቀደም ሲል አሳይተውት በነበረው የዘረኝነት ድርጊት ምክንያት ብሔራዊ ቡድኑ ሦስት ጨዋታዎችን በዝግ ስታዲየም እንዲያደርግ ወስኖ ነበር።
ነገር ግን የሐሙስ ዕለቱ ጨዋታ በፊፋ አማካይነት የሚደረግ በመሆኑ የዩኤፋ ውሳኔ ተግባራዊ ሳይደረግ ደጋፊዎች በስታዲየም ተገኝተው ጨዋታውን ለመከታተል ችለው ነበር።
የአውሮፓ የእግር ኳስ ማኅበር በሃንጋሪ ላይ ቅጣት ጥሎ የነበረው ባለፈው ሰኔ ወር ላይ በነበረ ጨዋታ ወቅት ካጋጠሙ የዘረኝነትና የመድልዎ ተግባራት ጋር በተያያዘ ነበር።












