የእንግሊዝ ተጫዋቾች በድጋሚ የዘረኝነት ጥቃት ሰለባ ሆኑ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እንግሊዝ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ሀንጋሪን 4ለባዶ ባሸነፈችበት ጨዋታ ጥቁር ተጫዋቾች ላይ የደረሰውን የዘረኝነት ጥቃት እንደሚያወግዙ የቡድኑ አባላት አስታውቀዋል።
ለማንችስተር ሲቲ የሚጫወተው ረሂም ስተርሊንግ እና ለጀርመኑ ዶርትመንድ የሚጫወተው ጁድ ቢሊንግሀም ናቸው የዘረንነት ጥቃት የደረሰባቸው።
የሀንጋሪ ደጋፊዎች በአውሮፓ ዋንጫ ወቅት ያሳዩትን ተገቢ ያልሆነ ባህሪ ተከትሎ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ብሄራዊ ቡድኑ በሜዳው የሚያደርጋቸውን ሶስት ጨዋታዎች ያለ ተመልካች በዝግ ስታዲየም እንዲያደርግ ውሳኔ አስተላልፎ ነበር።
ነገር ግን ከእንግሊዝ ጋር በነበረው ጨዋታ 67 ሺ ተመልካቾችን ማስተናገድ በሚችለው የቡዳፔሽቱ ፑሽካሽ አሬና ውስጥ ጥቂት ተመልካቾች እንዲገቡ ተፈቅዶላቸው ነበር። ምከንያቱ ደግሞ ውድድሩን በበላይነት የሚቆጣጠረው ፊፋ ስለሆነ ነው።
የእንግሊዝ ተጫዋቾች ገና ጨዋታው ሊጀመር ሲል ተንበርክከው ዘረኝነትን የሚቃወም መልእክት ሲያስተላልፉ የሀንጋሪ ደጋፊዎች በጩሀት ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ነበር።
ምንም እንኳን የሀንጋሪ ተጫዋቾችና አሰልጣኙ ማርኮ ሪሲ ደጋፊዎቻቸው የአንግሊዝ ተጫዋቾች ማስተላለፍ የፈለጉትን መልእክት እንዲያከብሩ ቢጠይቁም የሚሰማቸው ግን አላገኙም።
"ዘረኝነትን በመቃወም ተጫዋቾቹ ሲንበረከኩ ጀምሮ ተቃውሞ እንደሚገጥመን አውቀን ነበር። ነገር ግን ይህን ማድረግ ለእኛ ትክክለኛው ነገር ነው'' ብለዋል የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኙ ጋሬት ሳውዝጌት።
የጨዋታው መጀመሪያ አጋማሽ ምንም ግብ ያልተቆጠረበት ሲሆን በሁለተኛው አጋማሽ ግን ራሂም ስተርሊንግ ለእንግሊዝ የመጀመሪያዋን ግብ ሲያስቆጥር የሀንጋሪ ደጋፊዎች በከፍተኛ ሁኔታ የፕላስቲክ ብርጭቆዎችን ጭምር ወርውረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የማንችስተር ዩንይትዱ ተከላካይ ለእንግሊዝ ሶስተኛዋን ግብ ሲያስቆጥር ደግሞ የሀንጋሪ ደጋፊዎች ተቀጣጣይ ነገር ወደ ሜዳው ሲወረውሩ ተስተውለዋል።
የእንግሊዙ አሰልጣኝ ጋሬት ሳውዝጌትም ቢሆን ከዚህ አላመለጠም ነበር። ከጨዋታው በኋላ አሰልጣኙ ለጋዜጠኞች መልስ በሚሰጥበት ወቅት የበረዶ ስባሪ ከተመልካቾች ተወርውሮበታል።
"እንደ ቡድን ለየትኛው ጉዳይ አንድ ላይ መቆም እንዳለብን እናውቃለን። የተፈጠረው ነገር በየትኛውም መመዘኛ ተቀባይነት የለውም። የቡድናችን የደህንነት ኃላፊው ሁሉንም ተጨዋቾች አነጋግሮ መረጃ ሰብስቧል። ከዚህ በኋላ ማድረግ የሚገባንን ትክክለኛውን ነገር እናደርጋለን'' ብለዋል አሰልጣኙ።
"አንዳንድ ተመልካቾች በተንቀሳቃሽ ስልክ ጭምር ተገቢ ያልሆነ ነገር ሲያደርጉ እና ሲናገሩ ተቀርጸዋል። በተገቢው መንገድ እንርምጃ እንደሚወሰድ ተስፋ አደርጋለው'' ሲሉም አክለዋል።
የእንግሊዙ አምበል ሃሪ ኬን በበኩሉ ''ጓደኞቼን አነጋግራቸዋለሁ። በትክክል ሪፖርት እናደርገዋለን። በተገቢው መንገድ ጠንከር ያለ እርምጃ እንደሚወሰድ ተስፋ አደርጋለሁ'' ብሏል።
የእንግሊዝ እግር ኳስ ማህበር ባወጣው መግለጫ ደግሞ "የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾች ቡዳፔሽት ውስጥ የዘረኝነት ሰለባ መሆናቸው በጣም አሳዝኖናል'' ብሏል።
"ፊፋ ጉዳዩን በደንብ እንዲመረምረው እንጠይቃለን። ተጫዋቾቻችን እና የቡድ አባላት በሙሉ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። እኛም ይህንኑ እናደርጋለን። ዘረኝነትንም እየተቃወምን እስከመጨረሻው ድረስ እንታገላለን።''












