በቢሊየነሩ ብራንሰን የጠፈር ጉዞ በተፈጠረ 'ስህተት' ቀጣይ ጉዞዎች ተቋርጡ

የፎቶው ባለመብት, Virgin Galactic
ሰር ሪቻርድ ብራንሰን በቅርቡ ወደ ጠፈር ባደረጉት ጉዞ ወቅት የተፈጠረው ስህተት እስኪመረመር ድረስ የቨርጂን ጋላክቲክ አገልግሎት እንዳይሰጡ የዩናይትድ ስቴትስ የፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር (ኤፍኤኤ) ወሰነ።
ብሪታንያዊው ቢሊየነር ሐምሌ 11 በግል ሮኬታቸው ወደ 86 ኪሎ ሜትር ከፍታ በመምዘግዘግ የዕድሜ ልክ ምኞታቸውን አሳክተዋል።
ሆኖም ኒው ዮርከር መጽሔት ሮኬቱ አስቀድሞ ከተስማማበት የአየር ክልል ውጪ ለተወሰነ ጊዜ እንዴት እንደበረረ አጋልጧል።
የሰር ሪቻርድ ኩባንያ የመጽሔቱ ያቀረበውን ዘጋባ አስተባብሎ ተከራክሯል።
ሰር ሪቻርድ ከምድር ከፍ ብሎ ሽቅብ የተምዘገዘጉበት ሮኬት ዩኒቲ ወይም 'ስፔስሺፕ ቱው' የምትባል ስትሆን በሠላምም ተመልሳ አረፋለች።
የአየር በረራ ተቆጣጣሪው አካል በአጭር መግለጫው "በስፔስፖርት አሜሪካ ኒው ሜክሲኮ ግዛት ውስጥ የተከሰተውን የሐምሌ 11ዱን የስፔስሺፕ ቱው ጥፋት" ምርመራን በበላይነት እየመራሁ ነው ብሏል።
"የመጨረሻውን የአደጋ ምርመራ ሪፖርት እስኪጸድቅ ወይም ከአደጋው ጋር የተዛመዱ ጉዳዮች በሕዝብ ደኅንነት ላይ ተጽዕኖ እንደማያሳድሩ እስኪረጋገጥ ድረስ ቨርጂን ጋላክቲክ ስፔስሺፕ ቱው ወደ በረራ ላይመለስ ይችላል" ብሏል።
ቨርጂን ጋላክቲክ ለተቆጣጣሪው ባለሥልጣን መግለጫ በሰጠው ምላሽ ለምርመራው ሙሉ ትብብር እያደረገ መሆኑን ለቢቢሲ ገለጿል።
እንደዚህ ያሉ ጉዳዮችን በከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጥና የወደፊት ተልዕኮዎች ላይ የአቅጣጫ መዛባት እንዳይከሰት እንዴት እንደሚከወን ለመወሰን እየሠራ ነውም ብሏል።
ኩባንያው በሚቀጥለው የሚደረገውን ምርምር ይፋ ያደረገ ሲሆን፤ ጉዞው መስከረም መጨረሻ ወይም ጥቅምት መጀመሪያ ላይ የታቀደ ቢሆንም የኤፍኤኤ የምርመራ ውጤትን መጠበቅ አለበት።
የኒው ዮርከር መጽሔት ሐተታ የተጻፈው በኒኮላስ ሽሚድሌ ሲሆን ከምድር ከባቢ በላይ ከፍ ብለው በክፍያ የሚሄዱ ተሳፋሪዎችን መውሰድ የሚችል ሮኬት ለመሥራት እንዲሁም ሰር ሪቻርድ ለሁለት አስርት ዓመታት ያደረጉትን ጥረት የሚያሳየውን መጽሐፍ የጻፈ ሰው ነው።
የሽሚድል ታሪክ እንደሚለው ሰር ሪቻርድ እና ሌሎች ሦስት የኩባንያው በያዘው የሐምሌው በረራ ላይ አብራሪዎች በጉዞ ወቅት ከተመደበላቸው ክልል ውጪ ስለመውጣታቸው ማስጠንቀቂያ ደርሷቸዋል።
ይህ ችግር ካልተስተካከለ 'ዩኒቲ' ወደ ግቡ መድረስ እንዳይችል ሊያደርገው ይችላል። ሽሚድል በኩባንያ ፕሮቶኮሎች በተመሳሳይ ማስጠንቀቂያዎች ወቅት መመለስ ቢገባቸውም አብራሪዎች ሽቅብ መምዘግዘጋቸውን ቀጥለዋል ብሏል።
ቨርጂን ጋላክቲክ ቀደም ሲል የኒው ዮርከር ጽሑፍን "ትክክለኛ ገጽታን የማይሰጥ" በማለት ውድቅ አድርጓል።

የፎቶው ባለመብት, Virgin Galactic













