የመጀመሪያው የጠፈር የቱሪዝም ጉዞ ቀን ተቆረጠለት

የፎቶው ባለመብት, VIRGIN GALACTIC
ቨርጂን ጋላክቲክ የተሰኘው ኩባንያ ባለቤት የሆኑት ሰር ሪቻርድ ብራንሰን ለንግድ አላማ ባስገነቧት ሮኬት የሚደረገው የመጀመሪያው ወደ ጠፈር የሚደረገው የቱሪስቶች ጉዞ በመጪው ሃምሌ 4 እንደሚሆን ቀን ቆርጠዋል።
ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ጊዜ ወስዶ በአሜሪካ ውስጥ ሲገነባ በቆየው በዚህ ሮኬት አውሮፕላን ጀርባ ሰር ሪቻርድ ተሳፋሪ ይሆናሉ።
ሮኬቱ 90 ኪ.ሜ. ወይም ከባህር ወለል በላይ 295ሺህ ጫማ ከፍታ ላይ የመውጣት አቅም አለው።
ሰር ሪቻርድ የጠፈር በረራ አገልግሎትን ከሳይንሳዊ ምርምር ጉዞ ውጪ ለንግድ ዓላማ ማስተዋወቅ ፍላጎቴ ነው ካሉ ሰንብተዋል።
ወደ 600 የሚሆኑ ግለሰቦች ወደ ጠፈር ሄደው ለመጎብኘት ቀብድ ከፍለዋል።
የድርጅቱ ባለቤት በቅርቡ የሚደረጉት ይህ ጉዞም ደንበኞቹ ቀሪ የቲኬት ዋጋውን ለመክፈል እንደተቃረቡ ያመለክታል። የአንድ ቲኬት ዋጋም እስከ 250 ሺህ ዶላር ይደርሳል።
"በእውነቱ ጠረፍ የሁላችንም ነው ብዬ አምናለሁ። ከ 17 ዓመታት የምርምር ፣ የምህንድስና እና የፈጠራ ሥራ በኋላ ይህ የንግድ ኢንዱስትሪ ዩኒቨርስን ለሰው ልጆች ለመክፈት እና ዓለምን ለመቀየር ዝግጁ ነው" ሲሉ ሰር ሪቻርድ ተናግረዋል።
"ጠፈርን ለሁሉም ተደራሽ የማድረግ ህልም ማለም አንድ ነገር ነው፤ ይህንን አስገራሚ ህልም በጋራ ወደ እውነት መቀየር ደግሞ ሌላ ነገር ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
ቨርጂን ጋላክሲን ከንግዱ ጋር ወደፊት ለማራመድ ፍጹም ቁልፍ የሆነው ደረጃም ባለፈው ሳምንት በፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር የንግድ የጠፈር በረራ ፈቃድ ማግኘቱ ነበር።
የጋላክቲክ ቡድኑ እሁድ ሐምሌ 4 ወደ ጠፈር ለመውጣት ቢያቅድም በአየር ሁኔታ ወይም በቴክኒካዊ ምክንያቶች ሊዘገይ እንደሚችል ተጠቁሟል።
ተልዕኮው እሑድ ከተፈጸመ ሰር ሪቻርድ በዚህ የጠፈር ቱሪዝም ተቀናቃኛቸውን ጄፍ ቤዞስ ላይ ውድድሩን ያጠነክሩባቸዋል ማለት ነው።
የኦንላይን ገበያ ባለቤቱ ቤዞስ በሮኬት ግንባታዎች ከፍተኛ ሀብት ያፈሰሱ ሲሆን በመጪው ሐምሌ ወር ወደ ጠፈር ለመጓዝ ማቀዱን አስታውቋል።












