በኒው ዚላንድ በፖሊስ ክትትል ስር የነበረ አክራሪ 'የሽብር ጥቃት' ፈጸመ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኒው ዚላንድ ፖሊስ ኦክላንድ በሚገኝ ሱፐርማርኬት ቢያንስ ስድስት ሰዎችን ወግቶ ያቆሰለ "አክራሪ" ተኩሶ መግደሉ ተገለጸ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ጃሲንዳ አርደርን ድርጊቱን "የሽብር ጥቃት" ያሉት ሲሆን ጥቃቱ የተፈጸመው በፖሊስ ክትትል ስር በነበረ ስሪ ላንካዊ ዜጋ መፈጸሙን ገልጸዋል።
ማንነቱ ያልተገለጸው ግለሰብ በስላሚክ ስቴት አሸባሪ ቡድን መነሳሳቱን ጠቅላይ ሚንሰትር አርደርን ተናግረዋል።
ፖሊስ ግለሰቡ ጥቃቱን በፈጸመ በ60 ሰከንድ ውስጥ ገድሎታል።
አርደርን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ "ዛሬ የተፈጸመው አጸያፊ፣ ጥላቻና ስህተት ነበር" ብለዋል።
ስለ ጥቃቱ በመስማታቸው "በፍጹም እንዳዘኑ" ገልጸዋል።
ጥቃቱ እንዴት ተከሰተ?
ጥቃቱ የተፈጸመው በአገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር ዓርብ ከሰዓት በኋላ ኦክላንድ ውስጥ በሚገኝ ሱፐርማርኬት ውስጥ ነው።
ጥቃት አድራሹ ከመደብሩ ትልቅ ቢላዋ ወስዶ መውጋት ጀመረ። የክትትል ቡድኖች በቅርብ ነበሩ።
አንድ የዓይን እማኝ ለዜና ማሰራጫው ስታፍ ኤንዜድ እንደገለጸው በወቅቱ ሱፐርማርኬቱ ከፍተኛ የሃዘን ድባብ ነበር።
የበይነ መረብ ቪዲዮዎች እንዳሳዩት የተኩስ ድምጽ ከመሰማቱ በፊት የተደናገጡ ሸማቾች ከሱፐርማርኬቱ ሮጠው ሲወጡ ያሳያል።
"[ሰዎች]እየሮጡ ነበር። ብቻ ይጮኻሉ። በጣም ይጮኻሉ፣ ፈርተዋል" ያሉት እማኙ አንድ አዛውንት ተወግተው መሬት ላይ ተኝተው እንዳዩ ተናግረዋል።
ስለ ጥቃት አድራሹ ምን እናውቃለን?
በሕጋዊ ትዕዛዛ ምክንያት ማንነቱ ሊገለጽ የማይችል ሰው እአአ በጥቅምት 2011 ነበር ኒው ዚላንድ የገባው።
እአአ በ2016 በብሔራዊ ደህንነት ተፈላጊ የሆነ ሰው እንደነበረ አርደርን ተናግረዋል።
ጥቃት አድራሹ ከሚያራምደው ርዮተ ዓለም የተነሳ በስጋት ምክንያት የማያቋርጥ ከፍተኛ ክትትል ሲደረግበት ነበር። በብዙ ኤጀንሲዎች የሚታወቅ እና በሽብር ክትትል ዝርዝር ውስጥም ነበር።
አርደርን እንዳሉት ግለሰቡ ጥቃቱን እስከፈጸመበት ቅጽበት ድረስ ለእስር ወይም ለመያዝ የሚዳርግ ምንም ዓይነት ወንጀል አልሠራም።
ስለ ሰውዬው ጥቃት ምክንያት ተጠይቀው "አይኤስአይኤስ ያነሳሳው ነው" ብለዋል።
ቅርብ ክትትል የሚደረግበት ግለሰብ በስድስት ሰዎች ላይ ጉዳት ከማድረሱ በፊት ለምን እርምጃ እንዳልተወሰደበት ጥያቄዎች ተነስተዋል።
"እንደ እውነታው ከሆነ አንድን ሰው 24 ሰዓት ክትትል ይደራጋል ሲባል ሁሌም አጠገባቸው መሆን አይቻልም። ሠራተኞቹ በተቻለ ፍጥነት ጣልቃ ገብተው ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ መከላከል ችለዋል" ብለዋል የፖሊስ ኮሚሽነሩ አንድሪው ኮስተር።
ኮስተር አክለው እንዳሉትም ጥቃት አድራሹ ክትትል እንደሚደረግበት ስለሚያውቅ ቡድኖቹ ውጤታማ እንዲሆኑ ርቀትን መጠበቅ አለባቸው።
እአአ በ 2019 በክራይስትቸርች በሚገኙ ሁለት መስጊዶች አንድ ነጭ የበላይነት የሚያምን ግለሰብ 51 ሙስሊሞችን የገደለበት የኒው ዚላንድ እጅግ አስከፊው የሽብር ጥቃት ነው።












