አሜሪካ ካቡል ውስጥ ጥቃት ላደረሰው ቡድን እቅድ የሚነድፈውን ግለሰብ ገደልኩ አለች

ካቡል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

የአሜሪካ ወታደራዊ ኃይል በካቡል አውሮፕላን ማረፊያ ከደረሰውን ፍንዳታ ጀርባ ባለው ቡድን ውስጥ ዕቅድ የሚያወጣ ነው የተባለ ግለሰብ በሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) አማካይነት እንደገደለ አስታወቀ።

አይኤስ-ኬ የተባለው ቡድን የኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) ክንፍ ሲሆን፤ በካቡል አውሮፕላን ማረፊያ ባደሰው ጥቃት ወደ 170 የሚጠጉ ሰዎች ሞተዋል።

ከተገደሉት ሰዎች መካከል 13ቱ አሜሪካውያን ወታደሮች መሆናቸው ተገልጿል።

ታሊባን ካቡልን ከተቆጣጠረ በኋላ በርካታ ሰዎች አገሪቱን ለቀው ለመውጣት ወደ አውሮፕላን ማረፊያው ሲጎርፉ ነበር። ባለፉት ሁለት ሳምንታት ከ100,000 በላይ ሰዎችን ማስወጣት ተችሏል።

አሜሪካ ወታደሮቿን ከአፍጋኒስታን ለማስወጣት ቀነ ገደብ የተቀመጠላት እስከ ቀጣዩ ማክሰኞ ድረስ ነው።

የማዕከላዊ ዕዝ አባል ካፒቴን ቢል ኧርባን እንዳሉት፤ ፍንዳታ ላደረሰው ቡድን እቅድ የሚነድፈውን ሰው ለመግደል የድሮን ጥቃት የተሰነዘረው ናንጋሀር በተባለ የአፍጋኒስታን ግዛት ውስጥ ነው።

ኢላማው የአይኤስ አባላት እንደነበሩና ንጹሀን ላይ ጉዳት እንዳልደረሰም ተገልጿል።

ሪፐር የተባለው ድሮን ከመካከለኛው ምሥራቅ ተወንጭፎ የአይኤስ አባሉ መኪና ውስጥ ከሌላ የአይኤስ አባል ጋር ሳለ መትቶታል።

ናንጋሀር በተባለችው ግዛት በርካታ የአይኤስ-ኬ አባላይ እንደመሸጉ ይነገራል።

ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን ባለፈው ሐሙስ በአውሮፕላን ማረፊያው ቦምብ ያፈነዱትን ጂሀዲስቶች አድነው እንደሚይዙ አስታውቀዋል።

"ይቅር አንላችሁም። ያደረጋችሁትን አንረሳውም። አድነን እንይዛችኋለን። ለተግባራችሁ ዋጋ እናስከፍላችኋለን" ብለዋል።

በቀጣይ ቀናት ካቡል ውስጥ ሌሎች ጥቃቶች ሊሰነዘሩ እንደሚችሉም ፕሬዘዳንቱ ጠቁመዋል።

ከዚህ በኋላም ጥቃት ሊደርስ ስለሚችል ዜጎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሜሪካ በድጋሚ ማስጠንቀቂያ ሰጥታለች።

አይኤስ-ኬ ወይም ኢስላሚክ ስቴት ኮራሳን ፕሮቪንስ አፍጋኒስታን ውስጥ ውስጥ ካሉ ጂሀዲስት ታጣቂዎች በአጠቃላይ እጅግ ጽንፈኛው እንዲሁም ነውጠኛው ነው።

ፍንዳታ ያደረሱት ሴቶችና ሕፃናት እንዲሁም ወንዶች ከአፍጋኒስታን ለመውጣት እየተጠባበቁ ሳለ ነበር። በጥቃቱ ሁለት የእንግሊዝ ዜጎች እና ልጅ ተገድለዋል።

5,000 የአሜሪካ ወታደሮች ከአፍጋኒስታን መውጣት የሚፈልጉ አፍጋኖችን ጉዳይ ለማስፈጸም ካቡል አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ይገኛሉ።

አንድ ስማቸው ያልተጠቀሰ ባለሥልጣን ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት በቀጣይ 48 ሰዓታት ውስጥ ከአፍጋኒስታን የሚወጡ የተለያዩ አገር ዜጎችን ለማሳለፍ እየሠሩ ነው።

የታሊባን አመራሮች ከአውሮፕላን ማረፊያው ክፍሎች ጥቂቱ በቁጥጥራቸው ሥር እንደሆነ ቢናገሩም፤ አሜሪካ ግን አሁንም አውሮፕላን ማረፊያው በቁጥጥሯ እንደሚገኝ አስታውቃለች።

አብዛኞቹ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን (ኔቶ) አገራት የአስቸኳይ ጊዜ በረራ አቋርጠዋል። ፈረንሳይም የአውሮፕላን ማረፊያው ደኅንነት የተጠበቀ ስላልሆነ በረራ አቁማለች።