ኤቨር ጊቭን፡ የሱዩዝ ቦይን ዘግታ ለቀናት የቆየችው መርከብ ከወራት በኋላ ወደ አገሯ ተመለሰች

ታትሟል

በመጋቢት ወር የሱዩዝ ቦይን ዘግታ ለቀናት የቆየችው ኤቨር ጊቭን የዕቃ መጫኛ መርከብ ባለፍነው ሳምንት ያለምንም ችግር ዘግታው በቆየችው የሱዩዝ ቦይ በኩል ወደ አገሯ ተመለሰች።

መርከቧ ከሜድትራኒያን ወደ ቀይ ባሕር ከሚጓዙ መርከቦች መካከል እንደነበረች እና በአውሮፓ ጭነቷን በማራገፍ አሁን በድጋሚ ወደ እስያ እያመራች መሆኗን የሱዩዝ ካናል ባለሥልጣን አስታውቋል።

ኤቨር ጊቭን በቦዩ ውስጥ መንቀሳቀስ አቅቷት በቆየችባቸው ቀናት አንድ ሰው ለሞት የዳረገ ከፍተኛ ርብርብ ከተደረገ በኋላ ነበር ከቦዩ የተላቀቀችው።

የግብፅ ባለሥልጣናት ቦዩ በመዘጋቱ የደረሰባቸው ካሳ እንዲከፈላቸው መጠየቃቸውን ተከትሎ ኤቨር ጊቭን ለተጨማሪ ሦስት ወራት በኢስማሊያ ቦይ አካባቢ ቆይታለች።

መርከቧ ለሦስት ተጨማሪ ወራት በኢስማሊያ ቦይ እንድትቆይ የተደረገችው በግብፅ እና ኤቨር ጊቭን ባለቤቶች መካከል የካሳ ስምምነት እስከሚደረግ ነበር።

የሱዩዝ ቦይ ባለሥልጣን በትዊተር ገጹ እንዳስታወቀው ኤቨር ጊቭን በሁለት ጀልባዎች እና በተቋሙ ከፍተኛ መሪዎች ታጅባ ቦዩን በማቋረጥ ወደ አገሯ ተመልሳለች።

መርከቧ ትናንት አርብ ከሰሜን ወደ ደቡብ ከተጓዙት 26 መርከቦች መካከል አንዷ ስትሆን ሌሎች 36 መርከቦች በተቃራኒ አቅጣጫ ሲጓዙ ነበር።

የስዊዝ ካናል ባለሥልጣንም "ምሥራቁን ከምዕራብ ጋር የሚያገናኘው በጣም አጭር እና ፈጣን መንገድ" በማለት መተላለፊያውን አሞግሰዋል።

በዓለማችን ካሉ ግዙፍ የጭነት መርካቦች አንዷ የሆነችው ኤቨር ጊቭን 18,300 ኮንቴይነሮችን በሮተርዳም፣ በፊሊክስቶዌ እና በሀምቡርግ በማራገፍ አሁን ወደ ቻይና እየተጓዘች ትገኛለች።

የካሳው መጠን ባይታወቅም በቦዩ ላይ ለደረሰው ጉዳት ብሎም መርከቡን ለማስለቀቅ ለተደረጉ ሥራዎች የግብፅ ባለሥልጣናት የጠየቁት 550 ሚሊዮን ዶላር በሂደት እንደተከፈለ ታውቋል።