በሊባኖስ ጉዳት ባደረሰው ፍንዳታ የተቆጡ ተቃዋሚዎች በጠቅላይ ሚኒስትሩ መኖሪያ ቤት ጥቃት ፈጸሙ

ፍንዳታው የተከሰተው ወታደሮች ከጥቁር ገበያ ነጋዴዎች የያዙትን ነዳጅ ሲያስተላልፉ ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ፍንዳታው የተከሰተው ወታደሮች ከጥቁር ገበያ ነጋዴዎች የያዙትን ነዳጅ ሲያስተላልፉ ነው
ታትሟል

ሊባኖስ ውስጥ የነዳጅ ማጠራቀሚያ ፈንድቶ ሞትና ጉዳት ካደረሰ በኋላ ተቃዋሚዎች በአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤት ላይ ጥቃት ፈጸሙ።

እሁድ ዕለት በደረሰው ነዳጅ ፍንዳታ 27 ሰዎች የሞቱ ሲሆን 79 ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል።

ይህንን ተከትሎም በርካታ ተቃዋሚዎች ናጂብ ሚካቲ ከሥልጣናቸው እንዲለቁ ጠይቀዋል። በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቤትም ላይ ድንጋይ በመወርወር ከፖሊስ ጋር ተጋጭተዋል።

ሚካቲ የተቃዋሚዎቹን ሐዘን እንደተረዱ የገለጹ ሲሆን "ተቀባይነት የሌለው ጥፋት" ያሉትን የተቃዋሚዎቹን ድርጊት አውግዘዋል።

የአገሪቱ ሠራዊት እንዳስታወቀው የነዳጅ ማጠራቀሚያው ፍንዳታ ያጋጠመው በአካር ክልል ወታደሮች ከጥቁር ገበያ ነጋዴዎች የያዙትን ነዳጅ ሲያስተላልፉ ነበር።

የፍንዳታው መንስኤ እስካሁን ግልጽ አይደለም፤ ነገር ግን በወቅቱ በነዳጅ ማጠራቀሚያው አካባቢ በርካታ ሰዎች ተሰብስበው እንደነበር ጦሩ አስታውቋል።

"ጦሩ ቤንዚኑን እያከፋፈለ እንደሆነ ሰማን፤ ሰዎችም ነዳጁን በጀሪካን ለመቅዳት ሲጎርፉ ነበር" ስትል እስማኤል የተባለ ወንድሟ በአደጋው ክፉኛ የተጎዳባት ማረዋ አል ሼይክ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግራለች።

ማርዋ አክላም ፍንዳታው የተከሰተው አንድ ሰው ላይተር ሲጠቀም እንደሆነ ከዓይን ምስክሮች መስማቷን ገልጻ፤ "ሌሎች ደግሞ 'በአካባቢው ተኩስ ነበር' ብለዋል" ብላለች።

"ሟቾቹ የዚህ ግድየለሽ መንግሥት ሰለባዎች ናቸው" ብላለች ማርዋ።

ከአንድ ዓመት በፊት በቤይሩት የተከሰተውን ፍንዳታ ተከትሎ አስተዳደራቸው ሥልጣን የለቀውና በፖለቲካ አለመግባባት ምክንያት በሌላ ያልተተኩት፤ ነገር ግን አገሪቷን በባለአደራነት የሚያስተዳድሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ሐሰን ዲያብ "ፍንዳታው አሳዛኝ አደጋ ነው" በማለት ሰኞ ብሔራዊ የሐዘን ቀን ሆኖ እንዲውል አውጀዋል።

ጦሩ በበኩሉ የአደጋውን መንስዔ እያጣራሁ ነው ብሏል።

በአል ቴሊል የነዳጅ ማጠራቀሚያው የነበረበትን ቦታ ባለቤትም በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ጦሩ አክሏል። የአካባቢው ነዋሪዎችም የግለሰቡ ቤት በእሳት እንዳቃጠሉት ተገልጿል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ እንዳሉት ከተጎዱት መካከል ሰባቱ በአስጊ ሁኔታ ላይ ናቸው

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ እንዳሉት ከተጎዱት መካከል ሰባቱ በአስጊ ሁኔታ ላይ ናቸው

በሊባኖስ የነዳጅ እጥረት ያለ ሲሆን፤ በዓለም በከባድ የምጣኔ ሐብት ቀውስ እየተፈተኑ ካሉ አገራት አንዷ ናት።

የአገሪቷ ገንዘብ የመግዛት አቅም ባለፉት ሁለት ዓመታት ወድቋል። ይህም በአገሪቷ ያለውን ግሽበት ከነበረበት የበለጠ አባብሶታል።

ባለፈው ሳምንት የአገሪቱ ማዕከላዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ እጥረት በማጋጠሙ የነዳጅ ድጎማዎችን ለማቆም ወስኗል።

መንግሥት በበኩሉ የነዳጅ ዋጋ መለወጥ የለበትም ሲል ውሳኔውን ተቃውሟል።

የፀጥታ አካላትም በነዳጅ ማደያዎችና በግለሰብ የነዳጅ ማጠራቀሚያዎች የተከማቸ ነው ያሉትን ነዳጅ ቅዳሜ እለት ማከፋፈል ጀምረዋል።

አብዛኞቹ ሊባኖሳውያን በግል ጀኔሬተር (ኃይል ማመንጫ) ላይ ጥገኛ በመሆናቸው የነዳጅ እጥረቱ በርካታ ሰዎችና ተቋማት በቀን ለሁለት ሰዓታት ያህል ብቻ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኙ አድርጓቸዋል።

እሁድ ዕለት ባጋጠመው ፍንዳታ የተጎዱ ሰዎችን የሚያክሙ አንዳንድ ሆስፒታሎችም መደበኛ የነዳጅ አቅርቦት ከሌለ ለመዝጋት ሊገደዱ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።