ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአየር ንብረት ለውጥ፡ ሐምሌ ወር በዓለም ታሪክ ሞቃታማው ወር ሆኖ ተመዘገበ
የአሜሪካ የፌዴራል ሳይንሳዊ እና የቁጥጥር ኤጀንሲ ያሳለፍነው ሐምሌ በዓለም ታሪክ ውስጥ እጅግ ሞቃታማው ወር ነበር ሲል አስታወቀ።
የሐምሌ ወር የመሬት እና የውቅያኖስ ወለል የሙቀት መጠን ተደምሮ 0.93 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ የተመዘገበ ሲሆን ይህም ከ20ኛው ክፍለ ዘመን አማካይ ሙቀት ከሆነው 15.8 ዲግሪ የበለጠ ነው።
የዓለም ሙቀት መለካት ከተጀመረበት ካለፉት 142 ዓመታት ወዲህ ይህ ከፍተኛው የሙቀት መጠን ነው።
ባለሞያዎች የክስተቱ ምንጭ የአየር ንብረት ለውጥ በረዥም ጊዜ እያስከተለ ያለው ተፅዕኖ እንደሆነ እያሳሰቡ ይገኛሉ።
የአሜሪካ ብሔራዊ ውቅያኖስ እና የከባቢ አየር አስተዳደር በመግለጫው ላይ በሐምሌ ወር የታየው ሙቀት "የማይስተካከል ልዩነት" ሲል ገልጾታል።
የተቋሙ አስተዳዳሪ ሪክ ስፒንድራድ "በአየር ንብረት ለውጥ ሁኔታ አዲስ ክብረ ወሰን [ሪከርድ] ማለት በጣም መጥፎው ቦታ ነው" ብለዋል።
"ይህ አዲስ ሪከርድ የአየር ንብረት ለውጥ ለዓለማችን ያስቀመጠውን እጅግ የሚያሳስብ ጉዞ ያሳያል" ሲሉም ሪክ አክለዋል።
ከዚህ ቀደም ትልቁ የሙቀት መጠን የተመዘገበው እ.ኤ.አ. በ2016 ሲሆን አዲሱ ደግሞ ከዚህ በ0.01 ሴሊሺስ ከፍ ያለ ነው። በሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ የመሬት ሙቀት ከአማካኙ "ታይቶ ወደማይታወቅ" 1.54 ዲግሪ ከፍ በማለት እ.ኤ.አ. በ 2012 ከተመዘገበው በልጧል።
በተመሳሳይ ሐምሌ ለእስያ አህጉርም በታሪክ ሞቃታማው ወር፤ እንዲሁም ከአውሮፓውያኑ ሐምሌ 2018 በኋላ የአውሮፓ ሁለተኛው ሞቃታማ ወር መሆኑን መረጃው ያሳያል።
የአሜሪካው ተቋም መግለጫ እንዲሁ በሐምሌ ወር ሌሎች ጉልህ እና ያልተለመዱ የአየር ንብረት ለውጥ አመላካቾችን መዝግቧል።
በተገባደደው ሳምንት መጀመሪያ የተባበሩት መንግሥታት "የአየር ንብረት ለውጥ በምድር ላይ ታይቶ የማይታወቅ ተፅዕኖ እያሳደረ ሲሆን አንዳንድ ለውጦች ለዘመናት በሚሊኒየም ወቅት ወደነበረው ሙቀት ለመመልስ የማይቻሉ" ሲል ሪፖርት ማውጣቱ ይታወሳል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ "ግኝቱ ለሰብዓዊነት ቀይ ማስጠንቀቂያ ነው" ብለዋል።
"አሁን ኃይላችንን አሰባስበን ከሰራን የአየር ንብረት ጥፋትን ማስቀረት እንችላለን። ግን የዛሬው ሪፖርት ግልፅ እንደሚያደርገው ለመዘግየት ምንም ጊዜ እንደሌለን ብሎም ምክንያቶችን ለመደርደር ቦታ ያለመኖሩን ነው" ብለዋል።
የሪፖርቱ አዘጋጆች እ.ኤ.አ. ከ1970 ጀምሮ ባለፉት 50 ዓመታት የታየው የዓለም ሙቀት ጭማሪ ባለፉት 2000 ዓመታት ውስጥ ከታየው የ50 ዓመት ጭማሪ የበለጠ ነው ሲሉም ገልጸዋል።