ታጣቂዎች በአፍጋኒስታን የመከላከያ ሚኒስትር መኖሪያ ቤት ላይ ጥቃት ፈጸሙ

ታትሟል

በአፍጋኒስታን ዋና ከተማ ካቡል በሚገኘው የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስትር መኖሪያ ቤት ላይ ታጣቂዎች ጥቃት ፈጽመው አራት ሰዎችን ተገደሉ።

በካቡል ከፍተኛ ጥበቃ ይደረግበታል ተብሎ በሚታወቀውና የዲፕሎማቶች መኖሪያ ሰፈር ውስጥ በሚገኘው የሚንስትሩ ቤት ላይ ታጣቂዎች በመኪና ላይ በተጠመደ የፈንጂ ጥቃት ካደረሱ በኋላ ተኩስ ከፍተዋል።

ሚንስትሩ ቢስሚላህ ካን መሐመዲ ጥቃቱ ሲፈጸም በመኖሪያ ቤታቸው አልነበሩም ተብሏል። የሚኒስትሩ የቤተሰብ አባላትም ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው ከመኖሪያ ቤቱ እንደወጡ ተዘግቧል።

ይህ ጥቃት የተሰማው በአፍጋኒስታን በርካታ ቁልፍ ከተሞች ውስጥ በታሊባን እና በአገሪቱ መንግሥት መካከል የሚካሄው ጦርነት በተቀጣጠለበት እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ግጭቱ በአስቸኳይ እንዲያቆም ጥሪ ባቀረበበት ወቅት ነው።

የፀጥታ ኃላፊዎች ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል በጥቃቱ አራት ሰዎች መገደላቸውን ተናግረዋል። የጣሊያን የህክምና በጎ አድራጎት ቡድን በበኩሉ በጥቃቱ የሞቱ አራት ሰዎች አስከሬንና 11 ቁስለኞች ካቡል ውስጥ ወደሚገኙ የህክምና ተቋማት መወሰዳቸውን ገልጿል።

"አትጨነቁ፣ ሁሉም ነገር ደህና ነው!" ሲሉ የመከላከያ ሚኒስትሩ መሐመዲ ከጥቃቱ በኋላ በትዊተር ገጻቸው ላይ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት "ጥቃቱ የታሊባንን የጥቃት መለያዎች በሙሉ የያዘ ነው" ሲል ገልጾታል።

ጥቃቱ ከተፈጸመ ከሰዓታት በኋላ የካቡል ነዋሪ የሆኑ በርካታ ሰዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በተጋሩ ቪዲዮዎች የታሊባንን ጥቃቶች በመቃወም በመንገዶች ላይ ድምጻቸውን ሲያሰሙ ታይተዋል።

ተመሳሳይ ተቃውሞዎች በቅርብ ቀናት ከባድ ውጊያ በተካሄደባት የሄራት ከተማም ሰኞ ዕለት ተሰምቷል።

በአገሪቱ የሚገኙ የበርካታ ግዛቶችን ከተሞች ለመያዝ ጥረት እያደረጉ ባሉት የታሊባን ኃይሎች ላይ ሕዝቡ እያሰማ ያለው ተቃውሞ በጥቃት ውስጥ ላሉት የአፍጋኒስታን የጸጥታ ኃይሎች የሞራል መነቃቃትን ፈጥሮላቸዋል ተብሏል።

ነገር ግን በመከላከያ ሚኒስትሩ መኖሪያ ቤት ላይ በአማጺያኑ የተፈጸመው ጥቃት ታሊባን የመንግሥት መቀመጫ በሆነችው ካቡል ውስጥ ሳይቀር ጥቃት የመፈጸም አቅም እንዳለው ያሳያል።