የቀድሞው ታዳጊ መረጃ አቀባይ 'ዋይት ቦይ ሪክ' ኤፍቢአይን በ100 ሚሊዮን ዶላር ከሰሰ

ሪቻርድ ወርሽ ጀር

የፎቶው ባለመብት, DAVID GURALNICK, THE DETROIT NEWS

የምስሉ መግለጫ, ሪቻርድ ወርሽ ጀር ኤፍቢአይን የከሰሰው ከእስር ከተለቀቀ ከአንድ ዓመት በኋላ ነው
ታትሟል

ቀደም ሲል የእሱ ታሪኮች የሆሊውድ ፊልም ልብ ወለድ ነበሩ። አሁን ደግሞ በአሥራዎቹ እድሜው ለኤፍቢአይ መረጃ ሰጭ የነበረው ግለሰብ አዲስ ታሪክ ይዞ ብቅ ብሏል።

ሪቻርድ ወርሽ ጁኒየር መረጃ አቀባይ ከነበረበት ጊዜ ጋር ተያይዞ በደል ተፈጽሟል በሚል በቀድሞ ኤፍቢአይ ወኪሎች እና ዓቃቤ ሕግ ላይ የ100 ሚሊዮን ዶላር ክስ መስርቷል፡፡

የ52 ዓመቱ ወሪሽ ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር በተያያዘ ለሦስት አስርት ዓመታት በማረሚያ ቤት አሳልፏል።

በ14 የተመለመለው ግለሰብ በዕድሜ ትንሹ የኤፍቢአይ መረጃ አቀባይ ነው ተብሎ ይታሰባል።

የተለቀቀበትን የአንድ ዓመት ክብረ በዓል አስመልክቶ በቤተሰቦቹ ተከቦ ማክሰኞ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ "ይህ የሕይወቴ ምዕራፍ እንዲዘጋ እፈልጋለሁ" ብሏል።

"ዋይት ቦይ ሪክ" በመባል የሚታወቀው ወርሽ የአጭር ጊዜ መረጃ አቀባይነቱ እና ጥፋተኛ ተብሎ መከሰሱ በዚሁ ስም እአአ በ2018 ፊልም እንዲሠራ ምክንያት ሆኗል።

ወርሽ ስሙ ቅጽል ስም እንዳልነበረ ገልጾ በተያዘበት ወቅት በመገናኛ ብዙኃን የተሰጠ ነው ብሏል።

የቀድሞው የዲትሮይት የፖሊስ መኮንኖች፣ ጡረታ የወጡ የኤፍቢአይ ወኪሎች፣ የቀድሞ የፌደራል ዓቃቤ ሕጎች እና የዲትሮይት ከተማ በክሱ ውስጥ ተካተዋል።

በኤፍ ቢ አይ የዲትሮይት ጽህፈት ቤት ቃል አቀባይ ክሱ እየታየ በመሆኑ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

ባለ 10 ገጽ ክሱ ላይ እንደተገለጸው ከሆነ ወርሽ ሴት ልጁ ከሚታወቅ የዕጽ ነጋዴ ጋር ትገናኛለች ያሉት አባቱ ኤፍ ቢ አይን ካነጋገሩ በኋላ ነበር ከፌዴራል የደህንነት ወኪሎች ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ መገናኘቱን የገለፀው።

በዲትሮይት የአደንዛዥ ዕጽ ቡድኖች ላይ መረጃ ለመስጠት ከኤፍ ቢ አይ ወኪሎች እና ከዲትሮይት የፖሊስ መኮንኖች ጋር አዘውትረው መገናኘታቸውን አስታውሷል።

"ለግብረ ኃይሉ መረጃ ሰጭ ባልሆን ኖሮ በጭራሽ ከአደንዛዥ ዕጽ ቡድን ጋር ወይም በማንኛውም ዓይነት የወንጀል ድርጊት ውስጥ ባልተሳተፍኩም ነበር" ሲል በመግለጫው ላይ አስታውቋል።

ከሕግ አስከባሪ አካላት ጋር ያለው ግንኙነት ከተጠረጠረ በኋላ በአካባቢው ወንጀለኞች የመግደል ሙከራ እንደተደረገበት ቢገልጽም ሥራውን ለመቀጠል "ተገዶ" ነበር።

ከሁለት ዓመት ከሕግ አስከባሪ አካላት ጋር ከሠራ በኋላ ወርሽ ከሌላኛው ወገን ጋር ተቀራረበ። በገንዘብ፣ በሴቶች እና በቁሳዊ ሃብቶች "እንደታወረ" እአአ በ 2015 ለጋርዲያን ተናግሯል።

ኮኬይን በመያዝ በ17 ዓመቱ ሚሺጋን ውስጥ ጥፋተኛ ተብሏል። የመረጃ ሰጪነት ሚናው በፍርድ ቤት ተቀባይነት ስላልነበረው ዕድሜ ይፍታህ ተፈረደበት።

"በተሳሳተ መንገድ ተጓዝኩኝ" ሲል ለጋርዲያን ተናግሯል። "በቀሪው ሕይወቴ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል ብዬ በማላውቀው መንገድ ላይ ተጓዝኩ" ብሏል ወርሽ።