ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ስለ ሞት ወግ፡ ከዝነኛው የባሕር ዳር አስለቃሽ ከአቶ ደርሶ ሙጬ ጋር
የዶ/ር አምባቸውን፣ የመለስ ዜናዊን፣ የአበረ አዳሙን ለቅሶ ያደመቁት ሥመ ጥሩ አስለቃሽ አቶ ደርሶ ሙጬ 'መተዳደርያዎ ማስለቀስ ነው ማለት ነው?' ሲባሉ ብዙም ደስ አይላቸውም።
የሚተዳደሩት በልብስ ሰፊነት እንደሆነ፣ ነገር ግን አስለቃሽነቱ ሕዝብን የሚያገለግሉበት አንድ የተከበረ የሞያ ዘርፍ እንደሆነ አበክረው ያስገነዝባሉ።
ለአስለቃሽነቱ ሞያ በእርግጥም ልዩ ቦታ ይሰጡታል።
'እንደው የአባቶቻችን ባሕልና ልማድ እንደዋዛ ሊጠፋ ይሆን?' እያሉ አብዝተው ይብሰለሰላሉ። ቢሆን ቢሆን እንደ አሸን በፈሉት የአገር ቤት ዩኒቨርስቲዎች በአንዱ 'አስለቃሽነት' በዲግሪ ቢሰጥ ሁሉ ደስታቸውን አይችሉትም።
ያ ካልሆነም እንዲያው በበጎ ፈቃድ ለትውልድ ተረካቢዎች አጭር ስልጠና ቢጤ መስጠት ይኖርብኛል ብለው የሚመለከተው ክፍል ይህን እንዲያመቻችላቸው ይጠይቃሉ።
"እንዲያው በተቻለ ሁሉ ሞያውን በነጻ ለወጣቶች ማሰልጠን እፈልጋለኹኝ" ብለውናል፤ ደጋግመው፣ አበክረው።
በባሕር ዳር በለተይም ፋሲሎ ሰፈር የማያውቃቸው የለም። ነዋሪዎች 'ጋሽ ደርሶ' እያሉ ደመቅ ያለ ሰላምታን ይሰጧቸዋል።
ምናልባትም አንድ ቀን ሞቴን የሚያደምቁልኝ ሰው እኒህ ናቸው ብለው ይኾን?
አቶ ደርሶ ሙጬ ለ19 ዓመታት ደከመኛ ሰለቸኝ ሳይሉ አስለቅሰዋል።
'ደህና ዋሉ?' 'ደህና አመሹ?' ያሏቸው ሰዎች ጭምር በደህና ሳይውሉና ሳያመሹ ወደ አይቀሬው ሞት ሲጓዙ አይተዋል። ማየት ብቻ ሳይሆን በክብር ሸኝተዋል፤ መሸኘት ብቻ ሳይሆን ለቅሷቸውን አድምቀዋል።
ለሚገባቸው ደግሞ ፎክረውላቸዋል፡፡ አቅራርተውላቸዋል፡፡ ሸልለውላቸዋል፡፡ ሞታቸውን የጀግና ሞት አድርገዋል፡፡
ጋሽ ደርሶ፣ በፋሲሎ ሰፈር ብቻም ሳይሆን በመላው ባሕር ዳር ዕውቅ ናቸው፡፡
ሰላምታ ይበዛባቸዋል፡፡ ሰዎች እሳቸውን ሲያዩ ደማቅ ሰላምታ የሚያቀርቡላቸው ቀናቸው ትዝ ስለሚላቸው ይሆን ? አይቀሬው ቀን፡፡ የተቆረጠልን ቀን፡፡ የማይረፍድ የማይቀድመው ቀን፡፡ ፍጡራንን ሁሉ እኩል የሚያደርገው ቀን፡፡
እሳቸውም ቢሆን "እኔን የማያውቅ በባሕር ዳር ወየት ይገኛል?" ይላሉ፤ በልበ ሙሉነት፡፡
ለሕዝብ በአስለቃሽነት ያበረከቱትን አስተዋጽኦ በእርካታ ያወሱታል፡፡
‹ሐዘንተኛን ካላጽናናን ምኑን አብረን ኖረነ…› ይላሉ፡፡
ሰው የባለእንጀራውን ሰርግ እንጂ ለቅሶ መቅረት እንደሌለበት አበክረው ያስገነዝባሉ፡፡
"ለቅሶ አቆራራጭ ነው፡፡ ሰርግ ብትቀር፡፡ መብል ነው የቀረብህ፡፡ ግማሽ እንጀራ ነው የቀረብህ፡፡ የሰው ለቅሶ ግን አትብላ፡፡ ነውር ነው፡፡" ይላሉ፡፡
ራስዎን ያስተዋውቁ ሲባሉም ለዚህ ይሆን ቀልጠፍ ብለው እንዲህ የሚሉ፡-
"ደርሶ ሙጬ፣ ከታመመ ደራሽ፣ ከተጎዳ አድራሽ፣ ለሞተ አልቃሽ፡፡ ፉከራ ቀረርቶም እሠራለሁ፡፡ ሁለገብ ነኝ፡፡"
ማንም ይመሰክርላቸዋል፡፡
አቶ ደርሶ ላለፉት 19 ዓመታት በሺህ የሚቆጠሩ ድንኳኖችን አድምቀዋል፣ ሺህ ሬሳ ሸኝተዋል፡፡ ለጀግና ሞት ፎክረዋል፣ አቅራርተዋል፣ ሸልለዋል፡፡ ለሚስኪኖች ልብን ሰርስሮ የሚገባ ሙሾን አውርደዋል፡፡ እንባ አራጭተዋል፡፡
ለመሆኑ እንባ ሲያራጩ እሳቸው እንባ ግድ ይላቸው ይሆን?
"ውይ ቅዱስ ሚካኤልን ቡቡ ነኝ፤ ሐዘንተኛን ሳይ አያስችለኝም፤ እንባዬ እንዲሁ ይንዠቀዠቃል…" ይላሉ፤ ልብ በሚነካ ድምጽ፡፡
እንዲያ እያሉ ራሱ እንባ እንባ ይላቸዋል፡፡
በባሕር ዳር፣ ቤዛዊት ማሪያም ኮረብታ፣ (ቀድሞ የአፄ ኃይለሥላሴ ቤተ መንግሥት የነበረ)…እዚያ ላይ ወጥተን ቁልቁል አባይን ከነ ግርማ ሞገሱ እያየን ስለጥቁሩ ሞት፣ ስለ ሙሾ፣ ስለ ፉከራና ቀረርቶ፣ ሽለላና እንዲያ የመሳሰሉ ጉዳዮችን አውግተናል፡፡
ወደዚያ እያቀናን በነበረበት ወቅት ግን ሁለት ነገር አስገረመን፡፡
አንዱ ስልካቸው እረፍት አልባ መሆኑ፡፡
ጋሽ ደርሶ ይህ ሁሉ ደንበኛ አላቸው ማለት ነው? ሞት እንዲህ ረከሰ ማለት ነው?
ሁለተኛው አስገራሚ ነገር የስልካቸው የጥሪ እሪታ (Ring Tone) አንጀት ሰርስሮ የሚገባ በዋሽንት የተበጀ፣ ሞያቸውን የሚያሳብቅ የሐዘን እንጉርጉሮ መሆኑ፡፡
"ከየት አመጡት ይህን የስልክ እሪታ?" ብንላቸው ጊዜ፣ ‹…ራሴው ነኝ ዋሽንት እየተጫወትኩ ቀድቼ ወደ ስልኬ የዶልኳት" አሉን፡፡
ከአቶ ደርሶ ሙጬ ጋር በባሕር ዳር ቤዛዊት ኮረብታ ላይ ትንሽ ሞት አምተነው እንመለስ፡፡ አጭር የሕይወት ታሪካቸውን እነሆ፡-
"..ደርሶ ሙጬ ነው የምባል፡፡ የተወለድኹ ጎጃም ነው፣ ምሥራቅ ጎዣም፣ ደጋዳሞ፡፡ ያደኩትም እዚያው ነው፤ አሁን የምኖር ባሕር ዳር ነው፡፡
አያቴ ዘንድ ነው ያደኩ፡፡ ራሴን ስችል ባሕር ዳር መጣሁ፡፡ በ26 ዓመቴ ነው ባሕር ዳር የመጣሁት፡፡
ማስለቀስ የጀመርኩ ግን በ31 ዓመቴ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ማቅራራት፣ መፎከርና መሸለል እንጂ ማልቀስ አላውቅም ነበር፡፡"
ጋሽ ደርሶ ለአሳደጓቸው አያታቸው ልዩ ፍቅር ነበራቸው፡፡ ምን ዋጋ አለው ታዲያ ድንገት ያ ክፉ ሞት ደርሶ ነጠቃቸው፡፡ ጋሽ ደርሶ ምናልባት ያን ጊዜ ይሆን መሪር ሐዘን ያዘኑት?
በሺዎች ቀብር ላይ ለ19 ዓመታት ሳይታክት የተገኘ ሰው፣ መሪር ሐዘኑ የቱ እንደሆነ ማወቅ መቼስ ማንንም ያጓጓል፡፡
"ከአያቴ ነው የወረስኩ፡፡ እንዴት ያለ ከመንገድ የወጣ አልቃሽ ነበር መሰለህ፡፡ እሱ እያረጀ ሲሄድ እኔ ብቅ አልኹ፣ እሱ ሙቶ ነው እኔ የተተካሁ፡፡ ገና የ7 ዓመት ልጅ አርጎ ወስዶ ለ13 ዓመት አሳደገኝ፡፡ እና ከእናት አባቴ በላይ አስበልጬ ነው የምወደው የነበረ፡፡
በጣም ነው ያዘንኹ ያን ጊዜ!
‹‹ምነው አባትዬ ምነው አባት ዓለም…››እያልኹ አነባኹለት፡፡
"ልበላ ነው እንጂ ለለቅሶም አልመጣሁ
ባልሞትክብኝና በጉዴ ባልወጣሁ" አልኩኝ
ደገምኹና ደግሞ…
"አባቴ አባዬ! ደንዳናው ገበሬ
እታዛህ ይገኛል የነቀዘ ፍሬ"
እያልኹኝ አምርሬ አለቀስኹኝ፡፡ እንደነገርኩህ አያቴን በጣም እወደው ነበረ፡፡ ያን 'ለታ አምርሬ ነው ያዘንኹ፡፡ እመብርሃንን…"
ጋሽ ደርሶ አንድ በአያሌው የሚያሳስባቸው ነገር አለ፡፡ የአስለቃሽነት ሞያ መዘንጋት ጉዳይ፡፡
እንዲሁ እንደዘበት ጠፍቶ እንዳይቀር ይሰጋሉ፡፡ ጋሽ ደርሶ ለአስለቃሽነቱ፣ ለሞያው ለራሱ ማልቀስ ይዳዳቸዋል፡፡
ነገሩ ምን ያህል እንደሚያሳስባቸው መረዳት የሚቻለው ልጆቻቸው አስለቃሽ እንዲሆኑ መመኘታቸውን ስንረዳ ነው፡፡
አንዳንድ ወላጅ ልጄ ሐኪም ብትሆን፣ ፓይለት ብትሆንልኝ እያለ እንደሚመኘው ጋሽ ደርሶ ሙጬ ግን ልጆቼ አስለቃሽ በሆኑልኝ ይላሉ፡፡
"አሃ ልክ ነዋ!! ከአባቶቻችን የቆየው ነገር መጥፋት የለበትም፡፡ ሽለላውም፣ ፉከራውም፣ ማስለቀሱም ቢሆን፡፡ያባት ደንቡማ መጥፋት የለበትም፡፡ ማንኛውም ነገር፡፡ ትወልድ መተካት አለበት፡፡ ልጄ አስለቃሽ ቢሆንልኝ ብዬ መመኘቱ መቼ ይቀራልና፡፡ህእ!"
ልጅዎ አስለቃሽ እንዲሆን ከልብዎ ነው የሚመኙት? ነው ወይስ እንደው ለጨዋታው ድምቀት ወይ እንደዚህ…የምር ልጅዎ አስለቃሽ…?
"የአባቱም አይደል! መርሳትማ የለበትም፡፡ እርግጥ ነው ሲያድጉ የኔን ሙያ የግድ ይያዙት አልልም መቼም፡፡ ግን አስለቃሽ ቢሆኑልኝ ብዬ አስባለሁ፡፡ ሦስት ልጆች አሉኝ፡፡ አንዲቷ መምህር ናት፡፡ ሁለቶች ገና ደቃቃ ናቸው፡፡ ሞያው እልም ብሎ ሸምጦ መጥፋት የለበትም ነው እኮ የምለው፡፡ ደግሞ መዘንጋት የሌለብህ እኔም'ኮ ከአያቴ ነው ሞያውን የወሰድኹ፡፡ ያሳደገኝ አያቴ የሞተ ዕለት ነው፣ ያንኑ ቀን ሞያውን የወረስኩ፡፡"
ለምን እናለቅሳለን ግን? ለቅሶ ምንድነው? ሰውን በለቅሶ ማጀብ ስሜት የሚሰጥ ነገር ነው? እንዲያው ከናካቴው አስለቃሽ አስፈላጊ ነገር ነው?
"እንዴታ! አስለቃሽ የተጎዳን ሰው ማስተዛዘን ማለት ነው፤ ያ ሰው ብቻውን እንዳያር ነው፡፡ ሦስት አራት ሆነን የምናስለቅሰው እኮ ሐዘንተኛ እንዳይጎዳ ነው፡፡ለሌላ አይደለም፡፡ እስቲ ስማው ይኼን እንዴት እንደሚያስተዛዝን…(ድምጻቸውን አሰልለው ማንጎራጎር ጀመሩ)
እናትና ጓሮ ሁለቱ አንድ ናቸው፣
ሚሰጡት አያጡ ምን ቢቸግራቸው፤
እናት ዓለም አልኳት ስሟን አሳንሼ ስሟን አሳንሼ፣
ዘጠኝ ወር አርግዛ ስጋዋን ለብሼ፤
እናት ዓለምዬ እናት ዓለምዬ!
ስለ ሕይወት ያልዎት ፍልስፍና ምንድነው፣ ጋሽ ደርሶ? ሞትንስ እንዴት ነው ማየት ያለብን?
"ከመጣ ቀለል ማድረግ ነው፡፡ የምታመር ከሆነ ሐዘን ትጨምራለህ፡፡ እንግዲያውስ እውነት ንገረኝ ካልኸኝ ለሰው ማዘንስ ሲታመም ሲቸገር ነው፡፡ ከሞተ ኋላ አይመለስ!
ማስለቀስ ታዲያ ምን ትርጉም ይሰጣል?
"…መጽናናት ነው እንጂ፡፡ ከድንኳን ተቀምጠን ለምንድነው የምንሳሳቅ፣ ለምንድነው ካርታ ምንጫወት ? ለመርሳት ነውኮ፡፡ እንጂ መሪር ሐዘን ካዘንማ ያለውን፣ያልሞተውንም ሰው ደገምነው ማለት ነው፡፡ ከሞተ ሞተ ነው፡፡ ምንስ ቢታዘን ይመለሳል? መሪር ሐዘን ይመልሰዋል ወይ? ንገረኛ! ይመልሰዋል?"
እሱስ አይመልሰውም፡፡
"እናሳ!"
እኔምልዎ ጋሽ ደርሶ! የሃብታምና የድሀ ለቅሶ አንድነቱና ልዩነቱ ምንድነው?
"የሃብታም ለቅሶ አሸርጋጁ ብዙ ነው፡፡ የድሀ ግን ቄሱም በሥርዓቱ አይፈታውም፡፡ አባክኖ ነው ወስዶ ሚጥለው፡፡ የሃብታ ሲሆን ግን በየመንገዱ እያቆመ ያሸበሽብለታል፡፡ ሃብታም ከሆነ (ሬሳውም) ሰዓት ይውላል፡፡
ማልቀስን ማዘንስ ለድሀ ነው ለኮረንጮ ለባሽ
ሃብታምማ ሲሞት ይወጣል ነጭ ለባሽ
ዐይኔን እኔን እናት፣ ሙላ ሙላይቱ ሙላ ሙላይቱ
ለአንድያሽ ነው ወይ የበላሽ መሬቱ
"ጋሽ ደርሶ!"
"አቤት!"
ሌላ ጥያቄ ልጠይቅዎ!
"ምን ገዶኝ!"
ለማያውቁት ሰው ግን እንደው የእንጀራ ጉዳይ ሆኖብዎ ማልቀስ ምን ስሜት ይሰጣል?
"ተው እንጂ! ይሄ እንጀራ አይደለም፡፡ ዝም ብለን ድሀ እናስተዛዝን ብለን ነው'ይ እያለቀስን ያለን፤ ይሄ እንጀራ አደለም፡፡ ሰፈር ላይ አጋጣሚ ሰው ሲሞት ዝም ብለን ነው ቀብረን የምመጣው፡፡ "
እውነትዎን ነው?
"እግዚያአብሔርን! እኔ ይሄን ሽታ (ሥራ) ብዬ አልይዘውም፡፡ ለምን በለኝ፡፡ እኔ ራሱ ፈራሽ አይደለሁ እንዴ?ምንም ቤሳቤስቲን ሳንቀበል በቀን በቀን ስንት ደሃ ነው ቀብረን የምንመጣ፡፡ ነገ እኔም ሐጅ ነኝ፡፡ ፈራሽ ነኝ'ኮ፡፡ ተውንጂ…!"
እና ገንዘብ አይቀበሉም?
"እኔ ገንዘብ ክፈሉኝ አልልም፡፡ ከሰጡኝ ነው'ይ!"
የነጻ አገልግሎት ሰጥተው ያውቃሉ?
"ምን ይላል ይኼ! ፋሲሎ አሁን ካለሁበት ቀበሌ ላይ አምስት ሳንቲም ተቀብዬ አላውቅም፡ ስልህ፡፡ እግዚአብሔርን ነው የምልህ፡፡ ድሀ ከሆነ የትም ቢሆን ሳንቲም አልቀበልም፡፡ ማንኛውም ሰው ድሀ ከሆነ አልቅሼ አስለቅሼ ነው የምመለሰው፡፡
ቆይ እንግዲያውስ ልንገህ! እዚህ አየር ኃይል ኪቢአዶች ላይ ተደውሎልኝ አንድ ሰው ሞቶ ሄድነ፡፡ ፎካሪ ጨምረን ሄድነ፡፡ሚሽቲቱ በወለደች በ15 ቀኗ ነው እሱ የሞተ፡፡ እኔ ግን የተቀበልኩትን ብር በሙሉ ሰጥቻት ነው የመጣሁ፡፡"
እውነትዎን ነው?
"ቅዱስ ሚካኤልን! እንዴ እኔምኮ ፈራሽ ነኝ፡፡ እኔምኮ ከምድር በታች ዋይ ነኝ፡፡ ገንዘብ ምን ያደርግልኛል? የሰው ልጅ ፍቅር ነው የሚጠቅመው፡፡ የድሀ ብር ምን ያደርግልኛል!?
እንደው ጋሽ ደርሶ ሌላ ጥያቄ ብጠይቅዎ መቼስ ቅር አይልዎትም አይደል?
"ኧረ እንዲያውም…"
የሬሳ ሳጥን ሻጭ ሥራ ቀዘቀዘ ይላል፡፡ እናንተስ 'ሰሞኑን ጭር አለ'ኮ ትሉ ይሆን? ሀቁን ይንገሩኝ!
"ተው እንጂ ወንድም ዓለም! ምን ያደርግልኛል! ገንዘብ ምን ላደርገው፡፡ የሰው ልጅ ይሙት ብሎ የሚጸልይ ካለ በጣም ነውረኛ ነው፡፡ ምንም አይጠቅምም፡፡ እግዚአብሔር በሠራው በአካሉ በጊዜው ይሞታል እንጂ! የሞተው ሰው እያሳዘነነ ነው'ይ የምናለቅስ! እንዴት ገበያ ጠፋ እንላለን?"
እና እንደ ሬሳ ሳጥን ሻጭ አይደለንም ነው የሚሉኝ?
"ተው እንጂ ወንድም ዓለም! የሬሳ ሳጥን ሻጭም እኮ ሥራ ጠፋ ካለ እሱ ሳጥኑን ሳይሸጠው እሱ ሊሄድበት ይችላል እኮ፡፡ እኔ ምመኝ…እንዲያው ምነው የሰው ልጅ እንደ አስፋልት ዕድሜው በረዘመና በኖረ!"
ሥራ ተደራራቢ መጥቶ ያውቃል? በተመሳሳይ ሰዓት ሰዎች በርከት ብለው ሲሞቱ እንዴት ነው ቅድሚያ የምተሰጡት፡፡ ቅድሚያ የሚያሰጥ መመዘኛ ካለ ማለቴ ነው፡፡
"ባሕር ዳር ስድስት ነን፡፡ ሦስቱን ወደ ሌሎች እንሰዳለን፡፡ ተከፋፍለን እንሠራዋለን፡፡"
የከፍተኛ ባለሥልጣናት ለቅሶ አስለቅሰዋል?
"አዎ! እዚህ የነ ዶ/ር አምባቸው ጊዜም ነበርኩ፡፡ የነ ተስፋዬ ጊዜም ነበርኩ፡፡ ለቅሶ ማለዳ ሲለቀስ አረፈደ፡፡ ፉከራና ሽለላ ላይ ያቅራራሁ እኔ ነኝ፡፡ ያውም በሞንታርቦ ነው የሠራሁለት፡፡
እንዴት ብለው አስለቀሱ?
"ዶ/ር አምባቸውን አጅሬን ያየው ሰው
እንደ ጥጋት በሬ መሀሉን ሲገምሰው"
ብዬ መጀመሪያ ያቅራራሁ እኔ ነኝ፡፡ የኮሚሽነሩ አበረ አዳሙ ፉከራና ቀረርቶ አልሠራሁም፤ ማስለቀስ ብቻ ነው ለሱ የሠራኹ፡፡"
እምባ ይወጣዎታል ግን?
"ውይ ውይ ውይ ውይ! በጣም ነው የማለቅስ፡፡
እውነትዎን ነው?
"እመብርሃንን!! በቃ የሟች ቤተሰብ ሳይ እንባ ነው የሚቀድመኝ፡፡ ለቅሶ ላይ ወይ ሕጻን ልጅ ታያለህ፡፡ ያ ጨቅላ ሲንቦጀቦጅ አንተስ አይተህ ይቻልሃል? ይቻልኻል ወይ ንገረኝ!"
"እሱስ አያስችልም፡፡"
"እናሳ!"
ግን አቶ ደርሶ! ከሐዘኖች ሁሉ የከፋው ሐዘን የማን ነው? የልጅ? የእናት? የአባት?
"ሁሉም አንጀት ቆራጭ ነው፡፡ አባትም ልጅም እናትም ሁሉም፡፡ አባትህ ከእናት በላይ የሚሆንበት ጊዜ አለ፡፡ እኔ ከእናቴ አባቴን ነው የምወድ፡፡ ግልፁን ነው የምነግርህ፡፡ እናቴ ገርፋ ስታባረኝ አባቴ ደልሎ ያመጣኝ ነበር፡፡ ሁሉ መሪር ሐዘን ቢሆንም አንዱን መቼም ቻል ታደርጋለህ፡፡ የማትችለው ነገር የለም፡፡ የሰው ልጅ እህል በልቶ የማይረሳው ነገር የለም፡፡"
የልጅ ሞት ግን ጥልቅና መሪር ነው ይባላል እኮ?
"ቢመርህስ እግዜሩ ካመጣው የት ትደርሳለህ? እንባህ ሄዶ ሄዶ ይገደባል መቼስ፡፡"
ጋሽ ደርሶ! ኑሮ ተወዷል፡፡እሳት ሆነ፡፡ ሁሉ ነገር እየጨመረ ነው፣ ሞት ብቻ ነው የረከሰው፡፡ እናንተስ ዋጋ አትጨምሩም?
"ምን ብለን እንጨምራለን፡፡ ኑሮን ሰው አንገብግቦት የለ፡፡ ያለው እንዳቅሚቲ ሊኖር ይችላል፡፡ ከሽንኩርትና ቲማቲም ያነሰ ግን ምን አለ? እሱኮ ነው ያቃተን፡፡ ኑሮ ቢያንስ ማሽላ 1ሺ 700 ነው፡፡ ዘይት ዛሬ 600 ብር ደርሶ ያለ ነው፡፡ ዘወር ብሎ ያየው አለ? ሸማቹ እኮ እያለቀ ነው ያለ፡፡ እኔ ማዝን ከታች ላሉ ነው፡፡ ቁርስ በልቶ ምሳ የማይደግም፡፡ ክፉ ጊዜ…" (ድንገት ስሜታዊ እየኾኑ መጡ)
ዋጋ ትጨምራላችሁ ወይ ነበር ጥያቄዬ?
"እኛ ባለንባት ነው እስከሁን ያለነው፡፡ ቅዱስ ሚካኤልን፡፡ 1ሺህ ብር ነው የምንሠራው፡፡"
በሰዓት ነው የምታስከፍሉት?
"በቃ እንደዋለ እንውልለታለን፡፡ ወላ እስተ ስምንት ቢውል እንውላለን፡፡ ድሀ ሆነን እንጂ ገንዘብ ባንቀበል የእግዚአብሔርን መንገድ እናገኝ ነበር፡፡ ድህነት ሆነና ምን ይደረጋል መቼስ" (ክፉኛ አዘኑ)
ጋሽ ደርሶ!
"አቤት!"
ውጭ አገር ለለቅሶ ተጋብዘው ያውቃሉ?
"ከዚች ክልል ውጭ አልሄድም፡፡ ደግሞ ይሄም ሥራ ኾኖ ይዞራል እንዴ? አይዞርም፡፡ወረታ፣ ጎንደር፣ ብናት፣ አዲስ ዘመን፣ ዘጌ፣ ዳንግላ፣ ደብረወርቅ፣ ብቸና እንሄዳለን፡፡ ከዚያ አናልፍም፡፡"
ቆይ ግን ጋሽ ደርሶ! ብቸና ድረስ የምትጠሩት ብቸና አስለቃሽ ጠፍቶ ነው?
"እኛ ከገባን በኋላ የተለየን ነና፡፡ የኛ ይለያል፡፡ እንዳውም ብዙ ደንበኛ ‹ቢዛ› ካርድ አዘጋጁልን ይሉናል፡፡ እሱን አዘጋጅተን ልንበትን ነው የምናስብ፡፡ ኮጲ እያረገ ይይዛታል፡፡ ባሕር ዳር 8 ነን የምንሠራ፡፡ ሴት አንድ አስለቃሽ አለች፤ እሷ ጋር ዘጠኝ ነን፡፡
አንደኛ ደረጃ የምንባለው ግን አራት ነን፡፡ እኔ፣ ጓዴ፣ ይታየውና አስናቀው ነን፡፡ በዚህ ክልል እኛ ነን አንደኛ ደረጃ፡፡ በተለይ ሞንታርቦ በምንይዝ ጊዜ ለአገር ነው የምናስጨንቅ፡፡"
ሞንታርቦም አለ እንዴ?
"በማይክ እናለቅሳለን እኮ፡፡ አሁን እሑድ በዚያ ነው ያለቀስን፡፡"
ጋሽ ደርሶ!
"አቤት?"
አንጀት አርስ የሚባል ለቅሶ አለ?
"ምንደው እሱ፡፡ አንጀት አርስ ለቅሶ ብሎ የለም፡፡ ማዘን ከሆነ ማዘን ነው፡፡ በቃ ይኸው ነው፡፡"
ማለቴ! ለቀስተኛው በኋላ ሲጽናና አንጀት አርስ ነበር ብሎዎት አያውቅም?
"እሱስ አዎ! እግዜር ውለታህን ይመልስልህ፣ ልጆችህን ያሳድግልህ የሚሉን አሉ፡፡"
ይልቅ ልጠይቅዎ! እስከ ዛሬ ስንት ሰው አስቀብረዋል! በ19 ዓመት አገልግሎት ውስጥ፡፡
"እሯ! ምኑ ይቆጠራል አንተዬ? ምኑን አመጣኸብኝ!"
2ሺህ? 3ሺህ? 5ሺህ?
"እንደዚያ በለው!ይኾን ይሆናል! ሰው እንደ ቅጠል ነው የሚረግፍ! በአንድ ሰሞን ኮረና መጣና 17 ሰው በአንድ ወር ሠራሁ፡፡ እኔ አልሰለችም፡፡ ለቅሶ ከተባለ መቼስ ለቅሶ ነው፡፡ በዚያ ላይ ባለቤቴም አስለቃሽ ናት፡፡"
እንዴ? ይኼን አልነገሩኝምኮ!
"እሷ ከእህቷ ነው የተማረች፤ እህቷ አስለቃሽ ነበረች፡፡ እናቷ ሞታ ነው ለቅሶ የጀመሩ፤ ዜጌና፡፡"
ለጄኔራል አሳምነው ጽጌ ተቀኝተዋል?
"አሳምነው ጥጌ የክልሉ በሬ፣ አሳምነው ጥጌ
ብጠቅሰው ብጠቅሰው
ዝግት ብሎ ቀረ፣ ይወጣል ያልኩት ሰው"
በኮሮና ለሞተ ምን ብለው ያስለቅሳሉ?
ጤና ጣቢያ ብንሄድ ወባ ነው ይላሉ፣
ሆስፒታል ብንሄድ ስኳር ነው ይላሉ፣
ክሊኒክ ብንሄድ ግፊት ነው ይላሉ፤ ኮሮና ይላሉ፣
አያድኑም እንጂ ስም ማውጣት ያውቃሉ፡፡
በሉ እንግዲህ ጋሽ ደርሶ፣ ጨርሰናል፡፡ ግን እንዲያው ከመለያየታችን በፊት፣ ሞትን በቅርብ ያውቁታልና ከሞት ጋር እንዴት ተግባብተን ነው መኖር የሚሻል?
"ሞት ምንም አደለም፡፡ ተራ ነገር ነው፤ እግዜር ከወሰደ ወሰደ ነው፡፡ከጠራ ጠራ ነው፡፡ በአንድ ሳምንት ፋሲሎ ሰፈር ብቻ እኮ 7 ሰው ቀብረናል፡፡ እረ እግዜሩ ታረቀን ብለናል፡፡
እባክን አምላኬ አንገትክን አትድፋ
አንተ ማረን እንጂ እኛ ብናጠፋ
እመቤቴ ማርያም ልጅሽን ተቆጪው
አንቺን እንዴት ጨነቀሽ አንድሽን ብታጪው
እና ምን ለማለት ነው፡፡ ፍቅር ነው የሚበጅ! የሞት መድኃኒት ፍቅር ነው፡፡
ጋሽ ደርሶ
"አቤት!"
በሞት ሳይሆን በሕይወት ያገናኘን!
"አሜን ልጄ! አሜን!"