ባይደን ከሩሲያ የበይነ መረብ ጥቃት በሚሰነዝሩ ላይ እርምጃ እንደሚወስዱ አስጠነቀቁ

ታትሟል

የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን አገራቸው ከሩሲያ የሚሰነዘሩ የበይነ መረብ ጥቃቶችን ለመከላከል "ማንኛውም አይነት እርምጃ" እንደምትወስድ ለሩሲያው ፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲን ነገሩ።

ዋይት ሐውስ እንዳለው፤ የበይነ መረብ ጥቃቶችን ለመመከት ሩሲያ ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ፕሬዘዳንቱ ገልጸዋል።

ሩሲያ የአሜሪካን የበይነ መረብ ጥቃት ውንጀላ አትቀበለውም።

የሩሲያ እና አሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ባለፈው ወር ጄኔቫ ላይ ከተገናኙ በኋላ ትላንት ደግሞ ለአንድ ሰዓት በስልክ አውርተዋል።

አሜሪካ መነሻቸው ሩሲያ ነው የምትላቸው የበይነ መረብ ጥቃቶች ቁጥር እየጨመረ ነው። ባለፈው ወር 1,500 ድርጅቶችን ያሽመደመደ የበይነ መረብ ጥቃት መሰንዘሩ አይዘነጋም።

ባይደን እና ፑቲን በስልክ ከተወያዩ በኋላ ለመገናኛ ብዙኃን ማብራሪያ የሰጡት ባይደን "ከሩሲያ የበይነ መረብ ጥቃት ሲሰነዘር በሩሲያ መንግሥት የሚደግፍ ባይሆንም እንኳን ከሩሲያ የተሰነዘረ ጥቃት በመሆኑ ብቻ የሩሲያ መንግሥት እርምጃ እንዲወስድ እንደምንፈልግ ለፑቲን ግልጽ አድርጌላቸዋለሁ። መረጃ እስከሰጠናቸው ድረስ እርምጃ መውሰድ አለባቸው" ብለዋል።

ሩሲያ ሆነው ጥቃት የሚሰነዝሩ መረጃ ሰርሳሪዎች ሰርቨር ላይ አሜሪካ ጥቃት ታደርሳለች? ተብለው የተጠየቁት ባይደን "አዎና" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ከመሪዎቹ የስልክ ውይይት በኋላ፤ አሜሪካ የበይነ መረብ ጥቃት ደርሷል ብላ ለሩሲያ መረጃ ሰጥታ እንደማታውቅ የፑቲን አስተዳደር አስታውቋል።

የፑቲን ቢሮ ባወጣው መግለጫ "ሩሲያ የበይነ መረብ ጥቃት ወንጀልን ለመከላከል ዝግጁ ናት። ነገር ግን ባለፈው ወር አሜሪካ ስለ በይነ መረብ ጥቃት መረጃ አላከችልንም" ተብሏል።

አንድ ስማቸው ያልተጠቀሰ ከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣን በበኩላቸው፤ ለሩሲያ ስለ በይነ መረብ ጥቃት በተደጋጋሚ መረጃ ተሰጥቷታል ሲሉ ለኤኤፍፒ ተናግረዋል።

አሜሪካ እና ሩሲያ የበይነ መረብ ጥቃትን በጋራ ለመመከት ከፖለቲካ ነፃ የሆነ ሙያዊና ዘላቂነት ያለው ግንኙነት እንደሚያስፈልጋቸው ሩሲያ ገልጻለች።

አሜሪካ እንደምትለው፤ ባለፉት ዓመታት ከተሰነዘሩ የመረጃ ምዝበራና ሌሎችም የበይነ መረብ ጥቃቶች መካከል በጣም የከፉት የተሰነዘሩት ከሩሲያ ነው።

የሩሲያ የደኅንት ክፍል ስለ ጥቃቶቹ መረጃ እንዳለውም አሜሪካ ታምናለች።

ባይደን እና ፑቲን በስልክ ሲወያዩ፤ ሁለቱ አገራት የበይነ መረብ ጥቃትን ለመከላከል መረጃ መለዋወጥ እንዲሁም መተባበር እንዳለባቸው መስማማታቸውን ባይደን ተናግረዋል።

"ውይይቱ በጥሩ ሁኔታ ነው የተካሄደው። ተስፋ ሰጥቶኛል" ብለዋል የአሜሪካው ፕሬዝዳንት።

መሪዎቹ ስዊትዘርላንድ ውስጥ ሲገኛኙ ካነሷቸው ነጥቦች አንዱ የበይነ መረብ ጥቃትን መከላከል ነበር።

ሆኖም ግን ከዚያ ውይይት በኋላ በሩሲያ ወይም በምሥራቅ አውሮፓ እንደሚገኝ የሚገመተው የመረጃ ሰርሳሪዎች ቡድን 'ሬቭል' ከፍተኛ ጥቃት ሰንዝሯል።

ይህ ጥቃት ከተሰነዘረ በኋላ ባይደን የበይነ መረብ ደኅንነት ጉዳይ ላይ እንዲያተኩሩ ጫና እየተደረገባቸው ነው።

ባለፈው ወር ሁለቱ መሪዎች ጄኔቫ ውስጥ ሲገናኙ፤ ባይደን ጥቃት ሊሰነዘርባቸው አይገባም ያሏቸውን 16 ዘርፎች ዝርዝር ለፑቲን መስጠታቸው ተዘግቧል።

በሌላ በኩል በሁለቱ መሪዎች መካከል የተደረገውን የስልክ ውይይት በጽሑፍ ያቀረበው ዋይት ሐውስ፤ መሪዎቹ በሶሪያ ሰብዓዊ እርዳታ ማቅረብ ስለሚቻልበት መንገድ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ጠቁሟል።

ይህም በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ውጥረት ረግቦ ለመተባበር ዝግጁ መሆናቸውን አመላካች ነው ተብሏል።