ቱኒዚያ ውስጥ ስደተኞችን የያዘ መርከብ ሰጥሞ 43 ሰዎች ሞቱ

ታትሟል

ቱኒዚያ ውስጥ አርባ ሶስት ስደተኞች ከአንዲት መርከብ ላይ ወድቀው መስጠማቸውን የቱኒዚያ ቀይ ጨረቃ ማሕበር አስታወቀ።

ስደተኞቹ ከሊቢያዋ የዙዋራ ወደብ ተነስተው የሜዲቲራኒያን ባሕር አቋርጠው ወደ አውሮፓ ለመሄድ ነበር የተነሱት።

መርከቧ ላይ የነበሩ ሌሎች 84 ሰዎች በተኒዚያ ባሕር ኃይል አባላት እገዛ ከመስጠም ተርፈዋል ሲሉ የቱኒዚያ ቀይ ጨረቃ ማሕበር ኃላፊ ሞንጊ ስሊም ተናግረዋል።

ሞቃቱ አየር በርካታ ስደተኞች ከሰሜን አፍሪካ ወደ አውሮፓ ለመድረስ የሚመጡበት ወቅት ነው።

መርከቧ ጉዞ የጀመረችው ሰኞ ምሽት ሲሆን ከግብፅ፣ ሱዳን፣ ኤርትራና ባንግላዴሽ የመጡ ስደተኞችን ይዛ ነው ወደ ግዙፉ ባሕር የዘለቀችው።

መርከቧ መሃል ባሕር ላይ መንቀሳቀስ ያቆመችው የሞተር ችግር ደርሶባት ነው ይላል የቱኒዚያ ቀይ ጨረቃ ማሕበር።

ከቱኒዚያዋ የዛርዚስ ወደብ በሕይወት ተርፈው የተገኙት ስደተኞች ዕድሜያቸው ከሶስት እስከ አርባ ዓመታት ይደርሳል ሲል የቱኒዚያ መከላከያ ሚኒስቴር።

የቱኒዚያ ቀይ ጨረቃ ማሕበር በሕይወት ለተረፉት ስደተኞች ምግብና መጠጥ ከሰጧቸው በኋላ የሚያርፉበት ቦታ ሲያፈላልጉ ነበር ሲሉ የመገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ሊቢያ ከአፍሪካ ወደ አውሮፓ ለመሻገር የሚፈልጉ ስደተኞች ትልቋ መዳረሻ ናት።

ነገር ግን ቱኒዚያም ሌላኛዋ ከአፍሪካ ሃገራት ወደ አውሮፓ ለመሄድ የሚሹ ስደተኞች መሻገሪያ ሃገር ሆናለች።