እንግሊዝ ዩክሬንን 4 ለምንም በመርታት ለግማሽ ፍፃሜ አለፈች

ታትሟል

እንግሊዝ ሮም ላይ በተደረገ ጨዋታ ዩክሬንን በሰፊ ጎል ልዩነት በመረምረም ወደ አውሮፓ ዋንጫ ግማሽ ፍፃሜ አልፋለች።

አጥቂው ሃሪ ኬን ሁለት ጎሎችን በማስቆጠር የተቺዎችን አፍ ማስከደን ችሏል።

ሶስተኛዋን ጎል ሃሪ ማክጓዬር ከሉክ ሾው የተሻገረችለትን ኳስ በጭንቅላቱ ከመረብ በመቀላቀል ማስቆጠር ችሏል።

የማንቸስተር ዩናይትዱ ሉክ ሾው ሁለት ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን በማመቻቸት ደምቆ አምሽቷል።

አራተኛዋን ጎል ያስቆጠረው ጆርዳን ሄንደርሰን ሲሆን ይህ ለሃገሩ ያስቆጠረው የመጀመሪያ ጎል ሆኖ ተመዝግቦለታል።

እንግሊዝ እስካሁን በ2020 የአውሮፓ ዋንጫ ጉዞዋ አንድም ጎል አልተቆጠረባትም።

ለዋንጫ ለማለፍ በሚደረገው ግጥሚያ እንግሊዝና ዴንማርክ በለንደኑ ዌምብሌይ ስታድዬም ረቡዕ ምሽት 4 ሰዓት ይፋለማሉ።

በምድብ ጨዋታዎች አንድም ጎል ያላስቆጠረው አጥቂው ሃሪ ኬን ከተቺዎች ትችት ቢወርድበትም አሠልጣኙ ጋሬዝ ሳውዝጌት በሱ ላይ ያላቸውን እምነት ማጣት አልፈለጉም።

እነሆ እሱም አሠልጣኙን ሳያሳፍራቸው በሁለት የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ሶስት ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል።

ሌላኛው በትላንት ምሽቱ ጨዋታ ደምቆ ያመሸው የግራ መስመር ተመላላሹ ሉክ ሾው ነው።

ሉክ ሾው በመከላከልም ይሁን ወደፊት እየገፋ ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን ወደ ተፋላሚ ቡድን ሳጥን በመጣል ለእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ወሳኝ ተጫዋች መሆኑን አስመስክሯል።

በትላንት ምሽቱ ጨዋታ ማንቸስተር ዩናይትድን ለመቀላቀል የተስማማው የ21 ዓመቱ ጄደን ሳንቾም ተሰልፎ ተጫዋቷል።

የቼልሲው ሌላኛው ወጣት አማካይ ሜሰን ማውንትም የምሽቱ ኮከብ ነበር።

አሠልጣኙ ሳውዝጌት ጃክ ግሪሊሽንና ፊል ፎደንን በተቀያሪ ወንበር ላይ ማስቀመጥ መርጠዋል።

ሳውዝጌት የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድንን በዓለም ዋንጫና በአውሮፓ ዋንጫ ወደ ግማሽ ፍፃሜ የወሰዱ ሁለተኛው አሠልጣኝ ሆነዋል።

ሶስቱ አናብስት በመባል የሚታወቁት እንግሊዞች በሰባት ጨዋታ አንድም ጎል ሳይቆጠርባቸው ታሪክ መፃፍ ችለዋል።

ማክሰኞ ዕለት ጣልያን ከስፔን፤ ረቡዕ ደግሞ እንግሊዝ ከዴንማርክ ለዋንጫ ለማለፍ ይፋለማሉ።