ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አንበሳ የሚያሳድገው ግለሰብ በቲክ ቶክ ምክንያት ተወረሰበት
ታትሟል
ቤት ውስጥ በህገወጥ መንገድ ተቀምጦ ሲታቀፍ ሲታጠብ የነበረ አንበሳ በማህበራዊ ድር አምባ ቪዲዮዎች በመታየቱ የካምቦዲያ ባለሥልጣናት ወርሰው ወስደውታል።
አንድ ቻይናዊ አንበሳውን ከውጭ አስገብቶ በዋና ከተማዋ ፐኖም ፔን በሚገኝ አንድ ቪላ ውስጥ እያሳደገው ነበር ብለዋል ባለስልጣናቱ።
ምርመራ በሚያዝያ ወር የጀመሩት 70 ኪሎ ግራም የሚመዝነውን አንበሳ ቲክ ቶክ ላይ ከተመለከቱት በኋላ ነበር፡፡
የ 18 ወሩ እንስሳ ወደ ዱር እንስሳት አድን ማዕከል እንዲዛወር ተደርጓል።
ባለቤቱ ህጋዊ እርምጃ ይወሰድበት እንደሆነ ባለስወልጣናቱ አላሳወቁም።
የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ኔት ፒክትራ ለኤ ኤፍ ፒ ዜና ወኪል እንደገለጹት በቲክ ቶክ ላይ በተጋሩ ምስሎች አንበሳው ታይቷል፡፡
"ሰዎች ብርቅዬ የዱር እንስሳትን እንደ የቤት እንስሳት የማሳደግ መብት የላቸውም" ብለዋል።
መንግሥታዊ ያልሆነው ዋይልድ አኒማል አሊያንስ የተባለ የእንስሳት አድን ድርጅት በፌስቡክ ገጹ ላይ "በመኖሪያ ቤት ያለው ሁኔታ ለዱር እንስሳ ተገቢ አይደለም" ሲል ጽፏል።
በተጨማሪም "የአንበሳው የውሻ ጥርሶች እና ጥፍሮቹ በመነቀላቸው የኑሮውን ጥራት በእጅጉ የሚቀንስ ነው" ብሏል።